ዝቅ በል – ኮነ ፍስሐ -Tsega.com

ዝቅ በል – ኮነ ፍስሐ -Tsega.com

ከየትኛውም ዘር ወይም አገር ብንመጣ ማንኛችንም ጌታ ኢየሱስ ያዘዛቸውን ትዕዛዛት፣ማለት ጠላታችንን ለመውደድ፣ጥፋታችንን ለመናዘዝ፣ ሌሎችን በፍቅር ለማቅናት፣ ለቤተክርስትያናችን ለመገዛትና የበደሉንን ይቅር ለማለት የተፈጥሮ ዝንባሌ የለንም። እንደውም በደመነፍስ በመመራት ተቃራኒውን ነው የምናደርገው። ይህም ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ብዙ ጊዜ ወደ ግጭት ይወስደናል። ሆኖም እነዚህን ውስጣዊ ድካማችንን እንድናሸንፍና የሚያስከትሉትን ግጭት በተገቢው መንገድ እንድናያቸው እግዚአብሔር መንገድ አዘጋጀልን፥ ይህ የእግዚአብሔር መንገድና መፍትሄም “ክርስቶስ ኢየሱስ ሃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” (1 ጢሞ 1:15) የሚለው የምስራች ወንጌል ነው። በወንጌል በኩል ፈተናን የምንቁዋቁዋምበትን፣ ለትዕዛዙ የምንገዛበትንና እርሱን የሚያከብር ሕይወት እንድንኖር የሚያስችል ኀይል እግዚአብሔር ሰጥቶናል።

ወንጌል የግጭት አያያዝ ዘዴያችንን ከደመነፍስ ውሳኔ አውጥቶ በስርነቀል ለውጥ ይቀይረዋል። የመጀመርያው ለውጥ በግጭት ውስጥ ወይም ስንጋጭ እግዚአብሔርን ማስከበር ቅድሚያችን ይሆናል። እንደውም በወንጌል አማካይነት ያስታራቂነት ሚናን በግጭቶች መሃል እንድንጫወት ጌታ ያስችለናል። በጸጋው ውስጥ በአክብሮትና በፍርሃት ከሆንን የራሳችንን ጥቅም በማሳደድ ከምናገኘው ይልቅ እግዚአብሔርን በማክበር የበለጠ ደስታ እናገኛለን።

ከሌሎች ጋር ስትጋጭና ሲበድሉህ እግዚአብሔርን ልታስደስተውና ልታከብረው የምትችለው እንዴት ነው? በተፈጥሮ ዝንባሌህ፣ በስጋዊነት በመመራት፣ የራስህን ፍርድና ጥቅም በመፈለግ ወይስ በክርስቶስ ባገኝኅው አዲስ ማንነት በመመላለስ?

ሂድና ከበደለህ ሰው ጋር ዝቅ ብለህ በመታረቅ እግዚአብሔርን አክብር!

ሉቃ 6:27 ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ።

ሉቃ 6:35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። 36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።

2 ቆሮ 10: 3 በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4 የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤

Tsega@Tsega.com

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *