ለወንድሜ ገዳይ እየሱሴን ሰጠሁት – ጌሤም መጽሔት

ለወንድሜ ገዳይ እየሱሴን ሰጠሁት – ጌሤም መጽሔት

ጌታን ያገኘሁት በአስከፊ እስር ቤት ውስጥ ታስሬ በህመም ለመሞት ተቃርቤ ሳለ ነው:: ጌታ በአስደናቂ ሁኔታ ተገልጦ ከበሽታዬ ፈወሶ አዳነኝ። ከእስር ቤት ስወጣም በአካባቢዬ ወደሚገኝ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሄጄ መስከረም 4 ቀን 1984 ዓ ም ጌታን ተቀበልኩ፡፡ ከአራት ዓመት የቃሉ ጥናትና የጸሎት ጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወንጌላዊ ሆኜ በ1991 ዓ.ም በከምባታና ሀዲያ ወንጌላዊት የአሺራ ቤተክርስቲያን ማህበረ ምዕመናን ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ክልል በመዞር ጌታን እና አማኞችን አገልጋይ ሆንኩ ፡፡ አንድ ቀን “ጌታ ሆይ አንተ ለእኔ ይህን ሁሉ ምህረት እንዳበዛህልኝ ይሰቅሉህ ለነበሩ ሰዎችም አንተ ምህረት እንደለመንክላቸው እኔም በዘመኔ ከአንተ የተቀበልኩትን ምህረት ለሰዎች ሁሉ እንዳደርግ እርዳኝ” ብዬ ጸለየኩ፡፡

በወቅቱ በመንፈሳዊ ህይወቴ ሙሉ በሙሉ ሌላ ሰው ሆኜ ተለውጬ ነበር። ወሰን በሌለው ደስታ ውስጥም እኖርና እፀልይ ነበር፡፡ ይህን የሰራልኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና በዚህ አስገራሚ የለውጥ ጎዳና እያለሁ ከእለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍ 22፡1 “ከነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሀምን ፈተነው” ይላል በእርግጥ እግዚአብሔር ማንንም በክፉ አይፈትንም ነገር ግን ከእናቴም ከአባቴም በላይ የምወደው ታናሽ ወንድሜ ድንገት እንደሚሞት ጌታ ተናገረኝ፡፡ ወንድሜ ተክለ ሰውነቱ ግሩም የሆነ ቁመና ያለው ጉልበታም ሲሆን በጌታ ነገር ግን ደካማ ነበር፡፡ ራሱን እንዲችልና በጌታ ቤት እንዲፀና በማሰብ ያለኝን ንብረት ሽጬ ሱቅ ከፍቼለት “እኔ የምሰብከው የክርስቶስ ወንጌል በአንተ ምክንያት እንዳይሰደብ በዚህ ሱቅ እየሰራህ ሰው ሆነህ ኑር”ብዬው ሰጠሁት። ልጁም በሁሉ ነገር አደገ፡ ተለወጠ፡ ሰውም ሆነ፡፡

ጥር አራት ቀን 1994 ዓ.ም አየለ ከሚባል ከጓደኛው ጋር ተጣላና ወዲያው አስታርቀዋቸው የነበረ ቢሆንም አየለ ግን አዘናግቶ ምሽት ላይ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሺንሺንቾ በምትባል በደቡብ ከተማ በአንድ ሆቴል እራት እየበሉ ሳሉ በስለታም ጩቤ ጭንቅላቱን ወግቶት አመለጠ፡፡ ወዲያው ከተማው በጩኸት ተበጠበጠ፡፡ እኔ በዚያች ተወልጄ ባደኩባት ከተማ በአንድ ለቅሶ ቤት ሀዘን ለተቀመጡ ሃዘንተኞች 1ኛ ተሰሎ 4፡18 “እርስ በእርሳችሁ በዚህ ቃል ተፅናኑ” የሚለውን ቃል እሰብክ ነበር፡፡ አገልግሎቴን ጨርሼ ወደ ሠፈር ስሄድ ከተማው ትርምስ ነው፡፡ ሰው ወደ ተከማቸበት ሄጄ ምንድነው ብዬ ሳጣራ የራሴ ወንድም ነው። ወንድሜ ምቴ በደም ተለውሶ ሲያጣጥር አገኘሁት። ልቤ ራደ  እጅግ እወደውና እንሰፈሰፍለት ስለነበር የማደርገው ጠፋኝ። “ምን ሆንክ አልኩት” እርሱም ‹‹ አልተረፍኩም አለኝ›› ወደ ወላይታ ሆስፒታል በጥድፊያ ወሰድነው ግን አልተረፈም። እዚያው አረፈና ሬሳ ይዘን ተመለስን፡፡

በወንድሜ ቀብር ሥርዓት ላይ ወንጌል ለመስበክ ቆምኩኝና ጠቅላላ ሕዝቡን ስለመገኘታቸው አመስግኜ እስቲ ወንድሜን የገደለውን አየለ ቡራቆን እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ በሉት አልኳቸው። እጅግ ግራ የሚያጋባ ነገር ሆነ። ሰው በሙሉ በሀይል አለቀሰ ግን ማንም ይቅር ብሎ ለመናገር የደፈረ አልነበረም፡፡ በድጋሚም እኔ የምሰብከው ጌታ ኢየሱስ ምህረት ያድርግልህ በሉት አልኩኝ፡፡ አሁንም ሕዝቡ እንቢ አለኝ፡፡ ሦስተኛ ጊዜ እሺ ባለበት ቦታ እግዚአብሔር ይያዝህ በሉት አልኳቸው። ድፍን ሕዝብ ከኃያ ሺህ የሚበልጠው ሕዝብ በአንድ ቃል እግዚአብሔር ይያዘው አለ፡፡ ሕዝቡ ምን ያህል መራራ እንደሆነበት በዚያ ተረዳሁና ጥቂት የመፅናናት ቃል ተናግሬ ፀልዬ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ወዲያውኑም ሟቹ ወንድሜን ወደ ቀብር ወሰድንና ቀበርነው፡፡

በሦስተኛ ቀን የወንድሜ ገዳይ እኔ ካለሁበት ሃያ አምስት ኪሎ ሜትር በምትርቅ ከተማ በፖሊስ ስለተያዘ ለቃጫ ቢራ ወረዳ ፖሊስ መጥታችሁ እንድትረከቡ ተብሎ ተደወለላቸው፡፡ በጊዜው የነበረው የፖሊስ አዛዥም እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክት ወደ ለቅሶ ቤት ላከልን፡፡ገዳዩን እስረኛም ይዞ ወንጀል ወደ ፈጸመበት አቅራቢያ እስር ቤት ለማምጣት ተወሰነ:: ነገር ግን ወደ እኛ ከተማ የሚያመጣው መንገድ በሁለት አቅጣጫ ነበርና የእኛ ቤት ወጣቶችና ቤተ ዘመድ ጎረምሳው ስብሰባ አድርገው፡ የሟች ልብስ ለብሰው በመንገድ ከነመኪናው እንፈጨዋለን ተባብለው አንዱ ቡድን ጫጫ የሚባል ተራራ ላይ ጠበቁት ሌላኛው ቡድን በአረካ ቢመጣ ብለው በመዞርያ አካባቢ እናስቀረዋለን ብለው ቦርካሻ ወደተባለ ሥፍራ ሄዱ። እኔ ግን ተዉ ብዬ የሰጠኋቸውን ማስጠንቀቂያ እንቢ ስላሉኝ ማታ ሶስት ሰዓት ወደ ወረዳው ፖሊስ አዛዥ ቤት ሄድኩ፡፡

ኣዛዡ በዚያ ሰዓት ቤቱ መሄዴ ገርሞት ‹እንኳን ደስ አለህ ጠላታችሁ ተይዞአል። አሁን ልናመጣው ነው አንተ ለምን መጣህ?› አለኝ እየተገረመ። የመጣሁት ስለእሱ መያዝ አይደለም ወንድሜ ምትኩ ሞቷል፡፡ እኔ ግን የወንድሜ ገዳይ አየለ እንዲሞት አልፈልግም አልኩት፡፡ የሟች ልብስ ለብሰው መንገድ ሊጠብቁት ወጣቶች ስለ አደሙ ነገ ልጁ በፖሊስ መኪና እንዳታመጡት ነገር ግን ከነገ ወዲያ በህዝብ ማመላለሻ ከገበያተኛ ጋር ቀላቅላችሁ በድብቅ አምጡና ጣቢያ አስገቡት ብዬ መከርኩት፡፡ መቶ አለቃው እውነተኛ ክርስቲያን ቢሆንም የሰማው ነገር ከአዕምሮው በላይ ሆነበት፡፡ እጅግም ተገረመና እሺ ሂድ በቃ እንዳልከኝ አደርጋለሁ አለኝ፡፡ ይህ ጌታ በውስጤ ያፈሰሰው የእርሱ አስደናቂ ቸርነት በከተማው ሁሉ ተወራ፡፡ ነገር ግን ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ገዳይ በፍርድ ቤት ቆሞ መግደሉን ሲክድ በነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ላይ ነበርኩኝና በጣም አለቀስኩ፡፡ እድሜ ልክ እስራት ሲፈረድበትም በጣም አዘንኩለት። ልቤ ተሰበረ የልቡ ድንዳኔ አሳዘነኝ፡፡ ምስክሮችና ቤተሰቦቼን ገና በመጀመሪያው ችሎት ቀን ወደ ቤት ሸኝቻቸው ብቻዬን ወደ ማረሚያ ቤት ሄጄ የምወደውን ወንድሜን የገደለውን አየለን ፈለኩት፡፡

ከእናቱና ከታላቅ እህቱ ጋር እስረኛ መጠበቂያ ሥፍራ ላይ አገኘሁት፡፡ እናቱና እህቱ ደነገጡ እሱም ፈራ። አንዳች ጉዳት ላደርስ እንደመጣሁ ጠርጥሮ ተጠነቀቀ፡፡ ወደ እርሱም በመቅረብ ወንድሜ አየለ ሰላም ለአንተ ይሁን ብዬ እጄን ዘረጋሁለት እርሱም እየተሳቀቀ ጨበጠኝ። አቅፌ ሳምኩትና አይዞህ እኔ ስለ ወንድሜ ደም ልከስህ አልመጣሁም ነገር ግን የምስራች ልነግርህ መጥቼአለሁ፡፡ ወንድሜ ሆይ!በአንድ ዘመን እኔም እስረኛ፣ አረመኔና ክፉ ሰው ነበርኩኝ ያን ማንነቴን የለወጠውና ሰው ያደረገኝ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱን በማመኔ ዛሬ ኩነኔ የለብኝም፡፡ አንተ አሁን በፍርድ ቤት ወንጀል ለመከላከል ብትክድም በጌታ ፊት ግን ንስሀ ግባ። ወንጀል መስራትህንም በመካድህ አዝኜአለሁ፡፡ ነገር ግን በምትኩ ሲኦል ከምትገባ ጌታን በመቀበል ንስሀ ገብተህ ብትመለስ የዘለዓለም ህይወት ታገኛለህ፡ መንግስተ ሰማይ አብረን እንገባለን፡ ከእኔ ጋርም የክርስቶስ ወንጌል ሰባኪ ትሆናለህ አልኩት፡፡ አየለ በሙሉ ቁመናው ወድቆ አለቀሰ። በአጠገቤ ያሉ እናቱም እህቱም አለቀሱ። እኔም አብሪያቸው አለቀስኩኝና አብሮ ከአየለ ጋር ለነበረው ተባባሪ እስረኛ ጭምር በሉ አሁን ጌታን ተቀበሉ አልኳቸው። አይዞህ አየለ አታልቅስ አልኩና በኪሴ ያለውን ትንሽ ብር ስንቅ ሰጥቼ ኢየሱስን አትርሳው ብዬ ተለየሁት፡፡ በዚያን ቀን የተደሰትኩትን ደስታና ሐሴት በሰርጌ ጊዜም አላገኘሁትም፡፡ እጅግ ደስ አለኝ ምክንያቱም ወንድሜን ይቅር ብየዋለሁና ኢየሱሴንም ለወንድሜ ገዳይ የጥልን ግድግዳ አፍርሼ መመስከር ችያለሁና የጌታ መንፈስ በኃይል ወረደብኝ፡፡

ለቤተሰቦቼም ማታ ለማጽናናት ሰበሰብኳቸውና በምሽት ፕሮግራም እንደዚህ አልኳቸው አሁን ምትኩ ሞቷል በቃ ቁረጡና እርሱት፡፡ በዘመኔ የሚገባኝን ሁሉ አደረኩለት ያለኝን ሁሉ ሽጬ ንብረቴን የከተማ ቤት መሥሪያ ቦታዬን ሁሉ ሸጬ ሱቅ ከፍቼ ሰጠሁት፡፡ ጌታ ኢየሱሴን መሥክሬ በጌታ እንዲበረታ የቻልኩትን ሁሉ አደርኩኝ ከዚህ በላይ ምን አደርጋለሁ ግን በቃ ሞተ፡፡ አሁን ግን አየለ ጌታን እንዲቀበል መስክሬለት መጥቼለሁ ጌታን ከተቀበለ ደግሞ እርሱ ወንድማችን ይሆናልና አልኳቸው፡፡ ቤተሰቦቼ ለጊዜው ደነገጡ፡፡ ግን በጌታ ያለኝን ሕይወቴንና አቋሜን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ተቀበሉኝ፡፡ ለአየለ ቤተሰብ የምህረት ፀሎት በጋራ እናደርጋለን ብዬ ከቂመኝነት ነፃ እንድንሆን ለመንኳቸው በተለይ ሶስተኛው ታናሼ የወንድሜን ደም እበቀላለሁ እያለ ጩቤ ይዞ ከአየለ ቤተሰብ አንድ ሰው ለመግደል ውጪ ይዞር ነበር ያድርም ነበርና ንስሀ ገብቶ ህይወቱን ከጌታ ጋር አስተካከለ፡፡

ለአየለ ጌታን በመሰከርኩለት በሦስተኛ ወሩ በሲሼልስ ሬድዬ መንፈሳዊ ጣቢያ አየለ ቡራቆ እስር ቤት ሆኖ በጌታ አባቴ ለሆነልኝ ለወ/ዊ ተመስገን ቶማስ ብሎ መዝሙር መረጠልኝ፡፡ ለእኔና ለቤተሰቤም የይቅርታ ደብዳቤ ፃፈልን። በጣም እየዘለልኩ ጌታን አመሰገንኩ፡፡ በ2000 ዓ.ም ወርልድቨዥን ኢትዮ የዱራሜ ቅርንጫፍ በዞን ማረሚያ ቤት ኮንፍራንስ አዘጋጅተው ለወንጌል አገልግሎት ስሄድ አንድ ሰው በኃይል ሲሰብክ በከተማ ሁሉ በድምጽ ማጉያ እስፒከር ይሰማል፡፡ እኔ ስለዘገየሁ ሌላ ሰባኪ በጊዜ ገብቶ ነው ብዬ አሰብኩና ደስ እያለኝ ወደ ማረሚያ ቤት ግቢ ትልቅ አዳራሽ /የንስሀ ቤተክርስቲያን/ የምትባለው   አዳራሽ ስገባ የመድረኩ ሰባኪ አየለ ቡራቆ ነበር፡፡

በጣም ደስ ብሎኝ ሳልቀመጥ በጉባዔ ፊት ላቅፈውና ልስመው ወደ መድረክ ስወጣ ወንድሙን ገድዬ ኢየሱስን የሰጠኝ አባቴ መጣ አለና አየለ  ወደቀ፡፡ አይዞህ ብዬ አቅፌ አነሳሁትና ሙሉ ምስክርነት ለጉባዔ ስናገር በሺ የሚቆጠሩ የህግ ታራሚ እስረኞች በኮንፍራንሱ ነበሩና ወድያው አስራ ሰባት ነፍሰ ገዳይና ልዩ ልዩ ወንጀል ያለባቸው ብድግ ብለው በጌታ አመኑ፡፡ በ2001 ዓ.ም በዚያ ማረሚያ ቤት ትልቅ ሥራ ጌታ ሠራ ። በ2003 ዓ.ም ተጠርቼ ነበር በሌላ ምክንያት ብቀርም አሁን ወንድሜ አየለ ቡራቆ፡ በጌታ ውድ ልጄና የከአጣ ዞን ማረሚያ ቤት የንስሀ ቤተክርስቲያን መሪና ወንጌላዊ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ውድ አንባቢያን ሆይ ቂም አርግዞ ጥላቻን ደርቦ፣ እርቅን ጠልቶ የአምልኮን መልክ ይዞ በረከቱ ተይዞ ከጌታ ጋር ተላልፎ ብዙ ሰው ይኖራል፡፡ ይህንን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እውነት እላችኋለሁ በጐልጐታ ላይ ጌታ ለእኛ የሰጠንን ምህረትና ይቅርታ እንዲሁም የክርስቶስን ሕይወት በኑሯችን እናሳይ፡፡ የሚምሩ ይማራሉና የእግዚአብሔር ልጅ መሀሪ እንደሆነ እኛም መሀሪዎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ፡፡ እኛ ቃሉን የምንታዘዝ ከሆንን እግዚአብሔር ደግሞ የማንችለውን ሁሉ የሚያስችል ጸጋ ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባባሉ ለወንድሜ አየለም የእግዚአብሔር ፀጋ እንዲበዛለት እንድንፀልይለት መልዕክቴ ነው፡፡

 

ፓ/ር ተመስገን ቶማስ – ከጌሴም መጽሔት ለ www.TSEGA.COM

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *