ሴቶች አስገረሙን- ከሳባ አስራት

ሴቶች አስገረሙን- ከሳባ አስራት

Tsega.com – ከሳባ አስራት – አብሪ መጽሔት ቁጥር 6: –

መገረም ወይም መደነቅ የሚፈጠረው በሁለት ምክንያት ነው፣ አንድም በጣም መልካም በሆነ ነገር አሊያም በጣም መጥፎ በሆነ ነገር – ማለትም በአዎንታዊና በአሉታዊ መልኩ። ለምሳሌ ያህል እውቀቱ ከሚጠበቀው በላይ በሆነ ሰው የምንገረመውን ያህል ከሚጠበቀው በታች የወረደ እውቀት ያለው ሰውም ሊያስገርመን ይችላል። እግዚአብሔር እራሱ መገረሙን የሚገልጹልን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፣ አንደኛው በኢሳ 59:16 ላይ ማንም ሰው ወደ እርሱ ባለመማለዱ ሲሆን (አሉታዊ በሆነ መልኩ) ሌላው ደግሞ 2 ተስ 1:9 ላይ በመከራ ውስጥ ሆነው በእርሱ በማመን በጸኑ ሰዎች ነው(በአዎንታዊ መልኩ)

በርዕሳችን ላይ “አስገረሙን” የተባለላቸው ሴቶች በአዎንታዊ መልኩ ግርምትን የፈጠሩ ናቸው። “አስገረሙን” የሚለውን ቃል የተናገሩት ደግሞ የጌታ ደቀ መዛሙርት ናቸው። ስለ እነዚህ የጌታን ደቀ መዛሙርት ያስገረሙ ሴቶች ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን “አስገረሙን” ከተባለላቸው ስፍራ በጣም ቀደም ብሎ ነው። እነዚህ ሴቶች ብዙዎችን ከማስገረማቸው በፊት እያንዳንዳቸው ከጌታ በተደረገላቸው ነገር እስኪበቃቸው ድረስ ተገርመዋል። ከአጋንንት እስራት፣ ከበሽታ፣ ከማሕበራዊ መገለል፣ ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነፃ ወጥተዋል።

የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና የምናገኘው ዋነኛ ሃቅ ደግሞ ሰው በጌታ ነፃ የሚወጣው ተፈትቶ እንዲያገለግል ነው፣ በግብጽ የነበሩ እስራኤላውያንን፣ የጴጥሮስን አማት ወዘተ መጥቀስ እንችላለን። እነዚህ ሁሉ ነጻ የወጡት ጌታቸውን ለማገልገል እንደሆነ ተጽፎ እናነባለን። በዚህ ጽሑፍ የምናነሳቸው አስገራሚ ሴቶችም ነጻ የወጡት ነጻ አውጪውን ለማገልገል መሆኑን ቅን ልቦናቸው ተገንዝቧል። ስለዚህም የክርስቶስን አገልግሎት ይደግፉ ነበር (ሉቃ 8:13)::

ስለነዚህ አስገራሚ ሴቶች ትንሽ ላዋያችሁ። ጊዜው በ33 ዓ ም ገደማ ይሆናል፣ በዚህ ወቅት በመላው እስራኤል፣ በተለይም በኢየሩሳሌም ትኩስ የቡና ወሬ ለመሆን የበቃ አነጋጋሪ ድርጊት እየተፈጸመ ነበር፣ ይህውም ያ በፍቅሩና በብርታቱ እነዚያን ምስኪን ሴቶች ጨምሮ ብዙዎችን ከተለያዩ እስራቶች የፈታ ደግ ጌታ በተቃዋሚዎቹ ተይዞ ግፍ እየተፈጸመበት ነበር። ብዙዎችን ከእስር ፈትቶ እርሱ መታሰሩ በጣም አስገራሚ ቢሆንም ሌላው የሚገርመው ነገር ግን የቅርብ ወዳጆቹ እንኳ ጥለውት መሰወራቸው ነው።
ይሁን እንጂ የተደረገላቸውን መልካም ነገር ያልዘነጉት እነዚህ ሴቶች ከገሊላ ድረስ እየተከተሉት በመከራውም ቀን ከእርሱ እንደማይሸሹ እያሳዩ ነበር፣(ማቴ 27: 55፣56) ታላቁ ወዳጃቸው ክርስቶስ አስቀድሞም እንደተናገረው ራሱን ለብዙዎች ቤዛ ለማድረግ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጥቷልና ምንም እንኳ ከአንገላቾቹ ሊድንበት የሚችልበት ኅይል ቢኖረውም ያን አላደረገውም። ስለዚህ ብዙ ግርፋት፣ ጥፊና ፌዝ ከተቀበለ በኋላ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ያውም አገር ካወቃቸው ሁለት አደገኛ ወንበዴዎች መካከል።
የአርማትያሱ ዮሴፍም በድፍረት ወደ ንጉሡ ጲላጦስ ገብቶ የኢየሱስን በድን እንዲሰጠው ጠየቀ። መጽሐፍ እንደሚነግረን እርሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር (ማቴ 27:57 58) ንጉሱም ፈቅዶለት ከወሰደው በኋላ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፣ ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው። ታድያ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም እነዝያ በጌታቸው ፍቅር ልባቸው የነደደ ሴቶች ወደ ሁዋላ ሳያፈገፍጉ ብቸኛ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ፈጻሚዎች በመሆን ይህንን ትዕይንት ከመነሻው እስከ መድረሻው ካዩ በኋላ ተነስተው ወደ መንደራቸው በታላቅ ሃዘን ተመለሱ።
የንጉስ ጲላጦስ ቢሮ ቀጥሎ ያስተናገደው የካህናት አለቆችንና ፈሪሳውያንን ነበር፣ እነርሱም ገብተው “ያ አሳች በሕይወቱ ሳለ በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ እንዳለ ትዝ አለን፣ ስለዚህ ተከታዮቹ ሬሳውን ሰርቀው ከሞት ተነስቷል ብለው እንዳያስወሩና ከፊተኛውም ስሕተት የሁዋለኛው እንዳይከፋ መቃብሩ በዘብ እንዲጠበቅ እዘዝ ብለው ጠየቁ፣ ንጉሱም ጠባቂዎቻችሁን አኑሩ ብሎ ፈቀደላቸው።

ሴቶቹ ግን ይህ ከባድ ትዕዛዝ በወጣበትና ሁኔታዎች ሁሉ እጅግ በሚያስፈሩበት ሰዓት፣አልፎ ተርፎም አብረዋቸው የነበሩት ደቀ መዛሙርት እንኩዋን በር ዘግተው ተቀምጠው ሳለ ሰንበት ካለፈ በኋላ በሳምንቱ መጀመርያ ጎህ ሲቀድ መቃብሩን ሊያዩ ሄዱ። ግን ለምን ወደ መቃብር መሄድ አስፈለጋቸው? ከጌታቸው ጋር ያቆራኛቸው ፍቅር በሞት ይደመደም ዘንድ ስላልፈቀዱ አይደለምን? እርሱን ከሰቀለው ዓለም ጋር ከመዝፈን ይልቅ በድኑን ሽቶ መቀባት ለመንፈሳቸው የሚበልጥ ዕረፍት የሚሰጥ እንደሆነ ተገንዝበዋል።

ሴቶቹ በእምነትና በድፍረት ወደ መቃብሩ መሄዳቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በሁዋላ እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ የማይታወቀውን ታላቅ የምስራች የመጀመርያ ተናጋሪዎች አደረጋቸው የክርስቶስን ትንሣኤ። በማራቶን ታሪክ እንደሚዘከረው የግሪኮችን ድል ለማብሰር አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ሮጦ ሲያበቃ የምስራቹን ተናግሮ ተዝለፍልፎ በመውደቅ የሞተው አርኪሜደስ ትልቅ ተናጋሪ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፣ ነገር ግን የትኛው የምሥራች ነው “ኢየሱስ ተነስቷል” የሚለውን ያህል ለሰው ልጆች መልካም ወሬ ሊሆን የቻለና የሚችል? እነዚያ ሴቶች ምንኛ ታድለዋል!!! አስቀድሞ በዳዊት መዝሙር 68:11 “እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፣ የሚያወሩት ብዙ ሴቶች ናቸው” ተብሎ የተጻፈው ይህንን ዜና ይሆን?
በሴቶቹ አንደበት የተነገረው ይህ ዜና ለዓለም የቀረበ የምሥራች ብቻ አልነበረም ደቀ መዛሙርቱንም ያባነነ ነበር። ለዚህ ነው “ሴቶች አስገረሙን” ብለው ለራሱ ለትንሣኤው ጌታ ሳያውቁት የተናገሩት፣ ሉቃ 24:22 ከዚህ በላይ ምን አስገራሚ ዜና አለ? ይህ ዜና ፈሪዎችን አደፋፍሯል፣ተንሸራታቾችን አጽንቷል፣ ሃዘንተኞችን አጽናንቷል፣ ዝንጉዎችን አንቅቷል። በአጠቃላይ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

እስኪ አሁን ወደ እኛ ሕይወትና ዘመን እንመለስ፣ እኛስ ዛሬ ብዙዎችን እያስገረምን ነው? (በበጎ ገጽታው ማለት ነው)መጽሐፍ ቅዱሳችን በሁሉም ርዕስ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ጽንፍ ላይ ያሉ ሰዎችን ያሳየናል፣ አማኝና ከሃዲ፣ ለጋስና ንፉግ፣ ትጉህና ታካች፣ ወዘተ። ስለ ሴቶችም ተመሳሳይ ጽንፎችን እናያለን፣ ከደቀ መዛሙርቱ ቀድመው የትንሣኤው ምስክር በመሆን “አስገረሙን” የተባለላቸው ሴቶች እንዳሉ ሁሉ “ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉ ሞኞች ሴቶች አሉ፣(2 ጢሞ 3:7) “ ማን ሊያገኛት ይችላል?” የተባለላት ልባም ሴት ያለችውን ያህል (ምሳ 31:10) አሳብ የላትም፣ አንዳችም አታውቅም “ የተባለባት ሰነፍ ሴትም አለች፣ (ምሳ 9:13) ስለዚህ የቱ ጋር ነን?
ይህ የሴቶች ወር ተብሎ የሚታወስበት ጊዜ እነዚያን አስገራሚ ሴቶች ለማሰብ አመቺ ጊዜ ነው። ዛሬ ዛሬ በሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማለት በሚቻልበት መልኩ በየሚድያው የሚወራው ወሬ የሚያስጨንቅ ነው። የኑሮ ውድነት፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ስደት፣ የጤና ስጋት፣ የፖለቲካ ትኩሳት፣ ለአብዛኛው ሰው ራስ ምታት ሆኗል፣ታድያ በዚህ ጊዜ “ሴቶቹ” የጌታን መምጣትና የማዳኑን የምስራች ይዘን ልንወጣ አይገባም ትላላችሁ?
ውድ እህቴ ሆይ፣ እስኪ ጥቂት ስለ ራስሽ ጊዜ ሰጥተሽ አስቢ፣ ከአፈጣጠርሽ ጀምሮ አስገራሚ ሰው ነሽ፣ግሩምና ድንቅ ሆነሽ ተፈጥረሻልና። በጌታ የተደረገልሽም ነገር በሙሉ አስገራሚ ነው። አሁን የሚቀርሽ በአንደበትሽም አስገራሚ የሆነውን የጌታን የምስራች አብስረሽ ብዙዎችን ማስገረም ነው። “ጌታ በእውነት ተነስቷል፣ ሞትና መውጊያውን ሰብሯል፣ የዲያብሎስን ስራ አፈራርሷል፣የመንግስተ ሰማያትን በሮች ከፍቷል፣ አዲስ ዘመንን አውጇል” ብለሽ የምታበስሪበት ዘመን ላይ ተደብቀሽ አታሳልፊ። እግዚአብሔር ለኢያሱ እንደተናገረው “ ገና ያልተወረሰ ምድር አለና” ኢያሱ 13:1

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *