መታደስና መለወጥ

መታደስና መለወጥ

ያለወትሮው ጥቂት መኪኖች ብቻ በሚታዩበት INTERSTATE 95 በሚባለው ሰፊ ጎዳና ላይ መኪና እየነዳሁ ነበር። አእምሮዬ የምሄድበትን የእለቱን ዋና ጉዳይ ትቶ ስለ ብዙ ነገሮች ያስባል። ስለ ገንዘብ፣ ስለ ልጆች፣ ስለ ስራ፣ ስለ ተለያዩ ነገሮች ሰፊ ሃሳቦችን በማምጣት ይዞኝ ይሄዳል። የወሩን ወጪዬን ይደምራል፣ በዚህ ወር ስንት እንደሚተርፈኝም ይቀንሳል። ዓመት በዓሉን ተከትሎ ብዙ ወጪዎች ስለበዙ የሚያስጨንቅና የሚያሳስብ የወጪ ነገር እያመነጨ ይታገለኛል። “በመጠን ኑሩ” ይላል ቃሉ እያልኩ እኔም እመልስለታለሁ። ስለ አልተከፈሉት ወርሃዊ ክፍያዎች (BILL) እያስታወሰ ሊያስጨንቀኝ ሲል፣ እኔ ደግሞ ተረጋጋ ጌታ ካለ ይከፈላል እያልኩ ራሴ ለእራሴ እየነገርኩት እንጉዋዛለን። አእምሮዋችሁ በማያገባው እየገባ መካሪ ለመሆን ሲሞክር አስጨናቂና አላስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ብዙዎቻችሁን ሳያጋጥማችሁ አይቀርም ብዬ አስባለሁ። የእኔም አእምሮ ያለወትሮው ብዙ አላስፈላጊ ምክሮችን ማፍለቅ ጀምሯል።
መኪናዋ በደመነፍስ እየተነዳች ነው። መኪና መንዳትን ስለተለማመድኩት ይመስለኛል ፍጥነት መጠበቅ ወይንም መስመር ጠብቆ ስለመንዳት ማሰብ ካቆምኩ ዓመታት አልፈውኛል። ሳላስብ ወይንም ሳልጨነቅ መኪና መንዳትን ከቻልኩ ዘመናት አለፉኝ። በጭራሽ መኪና ስነዳ አላስብም ማለት እችላለሁ። አላስብም ስል በቃ ለምጄዋለሁ እንደ መራመድ ሆኖልኛል ማለቴ ነው። ፍሬን ያዝ አትያዝ ብዬ ሳላስብ አእምሮዬ እራሱ ያደርገዋል። ስለዚህ ሃሳቤን በሙሉ ሌሎች ነገሮችን ማሰላሰል ላይ አድርጌ ወደ ተጠራሁበት ስፍራ ለመድረስ እገሰግሳለሁ። አንደኛው የማያስበው አእምሮዬ ክፍል መኪናውን ይቆጣጠራል ሌላው ደግሞ ስለ ኑሮዬ ከራሴ ጋር እየተሙዋገተ እጉዋዛለሁ። አእምሮዬ አንዳንዴ ይከራከረኛል አንድ አንዴ ደግሞ ፈራጅ ሆኖ በድካሜና በሌሎች ድካም ላይ ሊፈርድ ሲነሳ እንጣላለን። ዝም በል ልክ አይደለህም እለዋለሁ። አንዳንዴ ሊያስፈራራኝ ይሞክራል። “ይሄ በጎን በኩል የሚወጋህ ነገር እኮ”…ምነው ዝም አልከው…ዶክተርህን ማየት አለብህ…ይለኛል። ጥሩ ምላሽ ከሰጠሁት ዝም ይላል። በውስጤ ቃል ካለ ዝም ይላል። የእለቱ ሃሳቦች ግን በጣም ብዙ ነበሩ።
በድንገት ከሁዋላዬ ብልጭ ብልጭ የሚል የፖሊስ መኪና በሃይለኛ ድምጽ ይከተለኝ ጀመር። አይኖቼ ወደ መኪናዬ የፍጥነት መለኪያ ተመለከቱ…90 ማይል በሰዓት ያሳያል። ፍጥነቴን ቀነስ አድርጌ ለመሄድ ስሞክር ፖሊሱ ከመንገድ ወጥቼ እንድቆም ምልክት አሳየኝ። መኪናዬን ከመንገድ ወጣ አድርጌ ቆምኩ።
አእምሮዬ ከቅጣት ላመልጥ የምችልበትን ብዙ ዘዴዎችን ለፖሊሱ እንድነግረው ደረደረልኝ። እኔና አእምሮዬ መታገል ጀመርን። አእምሮዬ የሚያቀርብልኝን ዘዴዎችን ሁሉ በውስጤ ያለው መንፈሳዊ ሰው ደግሞ ውድቅ አደረጋቸው። በመጨረሻም አንገቴን ጎንበስ አድርጌ “ጌታ ሆይ ይቅር በለኝ ስለዚህ ከንቱ ዓለም በአእምሮዬ ሳሰላስል ህግ ጣስኩኝ፣ ይቅር በለኝ ሁለተኛ አላጠፋም” ብዬ አጭር ጸሎት ጸልዬ ቀና ስል ፖሊሱ ከመስኮቴ አጠገብ ቆሞ በአግራሞት ይመለከተኛል። የመንጃ ፈቃዴን እንድሰጠው ጠይቆ ተቀበለኝና ለምን እንዳስቆምኩህ ታውቃለህ የሚል ጥያቄ ጠየቀኝ።
ለፖሊሱም ለጌታ የተናዘዝኩትን ጥፋቴን በትክክል ነገርኩት። እርሱም የሄድኩበት ፍጥነት ሕጉ ከሚፈቅደው ፍጥነት በ11 ማይል የበለጠ መሆኑንና ስፍራው የኮንስትራክሽን ስፍራ በመሆኑ የሚገባኝ ቅጣት እጥፍ እንደሚሆን በማስረዳት መንጃ ፍቃዴን ይዞ ወደ መኪናው ተመለሰ። አእምሮዬ ያቀረበልኝን ከቅጣት ማምለጫ ዘዴዎች በሙሉ ውድቅ አድርጌ፣ ጥፋቴን በማመን ንስሃ በመግባቴ ደስ አለኝ። ከመናደድ ይልቅ ያለወትሮዬ በደስታ ተሞላሁ።
ንስሃ ግን አቅጣጫ መቀየርን ስለሚጨምር ይህን አእምሮዬን ማደስ እንደሚገባኝ ወሰንኩ። ፖሊሱ የቅጣት ቲኬቱን ጽፎ ጨርሶ መጣ። አስተያየት አድርጌልህ ቅጣቱን ቀንሼልሃለሁ። ሆኖም ጥፋተኛ መቀጣት ስለአለበት የሃምሳ ብር ትኬት ብቻ ሰጥቼሃለሁና እዝች ጋ ፈርም ብሎ የቅጣት ወረቀቱን ሰጠኝ። ወረቀቱን ፈርሜ፣ ኦፊሰሩን “THANK YOU! GOD BLESS YOU“ ብዬ ባረኩት፣ ቅጣቴን ተቀብዬ፣ እግዚአብሔርን በማመስገን ፍጥነቴን ጠብቄ እየነዳሁ ያሰብኩበት ደረስኩ። ያቅበታል ብዬ እንዲመራኝ የፈቀድኩለት አእምሮ ጠባቂ ወይንም መታደስ እንደሚያስፈልገው ተረዳሁ።
ሐዋርያው “በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ” ሲል አእምሮአችንን መታደስ እንደሚያስፈልገው በደንብ በመረዳት ነው። ፓውሎስ ከስጋ እና ከአእምሮ ጋር ያለውን ትግል በደንብ የተረዳ ሰው ነው። ከጌታ ቀጥሎ ድካማችንን ስለተረዳውና እሱም ስለአለፈበት ይመቸኛል።
ከላይ ባለው አጭር ትረካ ውስጥ በተደጋጋሚ ከማድረግ የተነሳ የለመድናቸውና የቀለሉን የሚመስሉን ድርጊቶችን ያለማስተዋል ስናደርጋቸው አደጋ ላይ ሊጥሉን እንደሚችሉ እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ድሮ መንፈሳዊ ሰው ከመሆናችን በፊት በአእምሮአችን የተቀረጹ አካሄዶችና አስተሳሰቦች መታደስ እንዳለባቸው ይመክረናል። የስነ ልቡና ተመራማሪዎችም መንፈሳዊውን አመለካከት በደንብ ባይረዱትም ይህንን ሳናስብ የምናደርጋቸውን ልማዶች በግማሽ ከሚያስበው የአይምሮ ክፍል (SUBCONSCIOUS MIND) ይፈልቃሉ በማለት ያረጋግጡልናል።
በአይምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ ማለት ለአንተ ወይም ለአንቺ ምንድነው? ራሴን ለራሴ ተላልፌ እንዳልሰጥ እጠነቀቃለሁ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አብሮህ ያለው ስጋህ ወይም አሮጌው ሰውና አስተሳሰብስ ያስቸግርሃል?
join us for discussion on Berea Teleconference, SAT Dec 3, 9:00 AM EST
(712) 432-3553 or (712) 832-5260 or (712) 832-5262 Code: 2484446#
በጌታ ፍቅር ሰላም ሁኑ የምላችሁ ኮነ ፍስሐ ነኝ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *