ብሶት የተቀላቀለበት ደብዳቤ ለሉሊት – በመኮንን አዳሙ

ብሶት የተቀላቀለበት ደብዳቤ ለሉሊት – በመኮንን አዳሙ

እርግጠኛ ነኝ ደብዳቤዬ ሲደርስሽ ብዙ ነገሮች በዐይነ ህሊናሽ ተቀርጸው የኋሊት አጠንጥነሽ ብዙ ታስቢያለሽ። ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ የሚፈጥነው ጊዜ እንዴት እንደሚሮጥ ለራሴው ገርሞኛል። ከምትወጂያቸውና ከሚወዱሽ ተሰውረሽ የባህር ማዶን ሕይወት “ሀ” ብለሽ መኮምኮም ከጀመርሽ ያለፈው ግንቦት ድፍን አራት ዓመት ሞላሽ።
ባለፈው ሰኞ አንድ አሌክስ የሚባል የሚያውቅሽን ወንድም አግቼው ነበር። “ለመሆኑ ያቺ ሉሊት እንዴት ነች” ድሮ የነበራት የጌታ ፍቅር ደብዝዞባት ይሆን? ሲል እንደ መተከዝ ብሎ ጠየቀኝ። ደህና የመሆንሽን የምስራች አብስሬው ሳበቃ በብርቱ እንዲጸልይልሽ ግድ ብዬዋለሁ።
ከዓመታት በፊት በነበረን የወጣት አገልግሎት የነበረሽን ትጋት ስናስብ ሁሌም እንደነቃለን። ሰዓት አክባሪነትሽ፣ ለጸሎት የነበረሽ ጥማት፣ ለወንድሞችና እህቶች የነበረሽ ጠሊቅ ፍቅር፣የጠፉትን ፍለጋ የከፈልሽው ዋጋ ሁሉ ተደማምረው እንዳንረሳሽ አድርጎናል።
አይ የኔ ነገር! ሰላም ሳልልሽ ጭልጥ ብዬ ገባሁ አይደል? እኔ እምለው ጤንነትሽ እንዴት ነው? ህይወት በውጪ አገር ምን ይመስላል? እናንተ አገር ጊዜ በቀላሉ አይገኝም መሰለኝ የምትጽፊልን አሳቦችሽ እንደ ዘመኑ ቁምጣ አጥረውብኛል። ባለፈው ደውለሽ የችኮላ ሰላምታሽን በስልክ ሰምቼአት ነበር። እኔም የከበረውን ሰላምታሽን ለወዳጆቻችን ሁሉ አስተላልፌአለሁ። ወገኖች እንዴት ናቸው? ላልሺኝ መልሴ ደህና ናቸው፤ ደግሞም ደህናም አይደሉምም። መቼም ውስጥሽ አግራሞትን ሳይጭር አልቀረም።
በአጭር ቃል ሕይወታችን እየተዥጎረጎረ የት እንዳለን ለመለየት እስኪያስቸግረን ድረስ በሚያደናብር ነገር ውስጥ እያለፍን ነው። ይሄም ስልሽ ድሮ የነበረውን ሕይወት ሳይበርዙና ሳይከልሱ በጥንቃቄ የሚገቡና የሚወጡ ቅሬታዎች የሉም እያልኩ አይደለም። የብዙዎች ሕይወት ድርቅ እንደመታው አረማሞ ሲጠወልግ ይስተዋላል ለማየት ብዬ እንጂ። በእርግጥ አንድ ነገር አልደብቅሽም መሰባሰባችንን እንደ ወትሮው አላቆምንም እየተንገዳገድንም ቢሆን አለን፣ ነገሮች ግን ተለዋውጠዋል። በፊት የነበረን የጸሎት ሕይወት እያየነው ከእጃችን ወጥቷል፡ ጉልበታችንን በጌታችን ፊት ማንበርከክ የኪሊማንጃሮን ተራራ ከመውጣት ይልቅ ጠንክሮብናል። እንደምንም ብለን ተንበርክከን ለመጸለይ ስናስብ ጌታን በጸሎት የመፈለግ ረሃባችን ተወስዶ፣ ዘምረን ብቻ እንነሳለን። በእርግጥ በሕብረት ስንሰባሰብ “አለሁኝ” ለማለት ነው መሰል የጸሎቱን መዓት እናዥጎደጉደዋለን። እንቆቅልሹ ግን በግል ሕይወታችን መትጋት ያለመቻላችን ነው። ብዙዎቻችን ለእንቅልፍ እና ለድንዛዜ ተጋልጠናል። ሌሊት መጸለይ የሚባል ነገርማ ከተረሳ ዓመታት ነጉደዋል። ሌሊቱን ሙሉ አንኮራፍተን አድረን፣ ጥዋት ላይ “ በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን” ብሎ መፈትለክ ነዋ! ታድያ ሕይወት እንዲህ ሲሆን አይገርምም ትያለሽ? ክርስትናን ያለጸሎት ለመዝለቅ መሞከር ዝናብ ከሌለባቸው ደመናዎች በምን እንደሚለይ ለኔው ለራሴ ግራ ገብቶኛል።
ሌላ ትዕንግርት ደግሞ ልንገርሽ።ዘንድሮ አዲስ አበባ ብታይ የኮንፍረንስ ችግር የሚባል ነገር የለም። በየቤተ እምነቱ ፕሮግራሞች በሽበሽ ናቸው። አማርጦ መሄድ ይቻላል፤ ይህ በመሆኑ መድኀኒታችንን ልናመሰግነው ይገባል። የዚያኑም ያህልም በአማኙ ላይ ቀይ መብራት የበራ ይመስላል ። ምን ለማለት እንደፈለግሁ ሳይገባሽ አልቀረም። የኮንፍረንስ ደንበኛ የሆነው የአገሬ ወጣት ከየመድረኮቹ በሚወረወርለት የዕለት ስንቅ ብቻ እየታገዘ ኑሮን “ይህ ብቻ ነው” ብሎ መጉዋዝን አዘወትሯል። “አገልጋዮችን ያኑርልኝ” ብሎ ተማምሎ የወጣ ይመስል ሁሌም እነሱን ተስፋ ያደርጋል። እነሱ የሉም ማለት ሕይወቱ በቅጽበት አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። እያልኩ ያለሁት በግሉ ቃሉን የሚያጠና ፣ ምህረትን የሚቀበል እና ነፍሱን የሚመግብ ትውልድ እየጠፋ ነው።
ሉሊትዬ ባለፈው ምን ሆነ መሰለሽ የመጠበቅያ ግንብ አባላት የሚለውን የስህተት መጽሔት ተሸክመው የሚዞሩት ሰዎች ወይም “የይህዋ ምስክሮች” የምንላቸው በድንገት ከሕብረታችን አባላት ሁለቱን አግኝተዋቸው የማደናበርያ ናዳ ያወርዱባቸው ገቡ። የሃሰት አስተማሪዎቹ “እየሱስ ፍጥረት ነው” የሚለውን መርዝ የተቀላቀለበት ንግግራቸውን ሲያዥጎደጉዱት፣ ወጣቶቹ ደግሞ በተራቸው “ኢየሱስ አምላክ ነው እንጂ ፍጡር አይደለም!” አሉ። እንዲህ ማለታቸው ባልከፋ ነበር፣ ነገር ግን ኢየሱስ አምላክ ስለመሆኑ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጥቅስ አውጥታችሁ አሳዩን “ሲሉዋቸው የኛ የኮንፍረንስ ደንበኞች ለምን ማጣፍያው አያጥራቸው መሰለሽ። እንደመደናገጥ ብለው ጸጉራቸውን እያከኩ “ እ ቆሮንቶስ ላይ ወይንም ሮሜ ላይ ይሆናል” አሉና ከክርክሩ መሃል እራሳቸውን አስመለጡ። እነዚሁ ወጣቶች ባለፈው እሁድ በነበረን የወጣት አገልግሎት ላይ መጥተው “እኛ የምንለው፣ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የትጋ ነው ኢየሱስ አምላክ እና ጌታ ነው የሚለው?” ቢሉን ለምን ሁላችንም ግራ አንጋባም መሰለሽ። ያን ጊዜ ወንድማችን በላቸው እንደ ምንም ብሎ ኀይሉን በማሰባሰብ “ሮሜ 9፦5 1ኛ የኋንስ 5 ብሎ ሁለት ጥቅስ ሲወረውር ጊዜ ፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ጋር ለማመሳከር ሁላችንም ተሽቀዳደምን። ወይ አለመዘጋጀት! ለካስ መስማት ብቻ ሳይሆን እያነበቡ፣ እያጠኑ ለምንጠየቀው ሁሉ መልስ እንዲኖረን መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለን አሰብን። ዝም ብለን ኮንፍረንስ እያባረርን ስንዘል ለካስ ባዶ ቀርተናል። ከዛ በሁዋላ ግን ሁላችንም ሳቅ በሳቅ ሆንን። ለካስ ቃሉ ይሰብክልናል እንጂ ቃሉን በደንብ የት ላይ እንዳለ አናውቀውም።
ሉሊትዬ ዛሬ በልቤ ያለውን ሁሉ እያራገፍኩብሽ ነውና ትከሻሽን አስፍተሽ ተሸከሚው። ማን ያውቃል? እያወራሁ ባለሁት ችግር ውስጥ አንቺም ትኖሪበት ይሆናል። በአዲስ አበባ ያለን ወጣቶች ችግራችን የትየለሌ ሆኗል፣ የቱን ነግሬሽ የቱን እንደምተው አላውቅም፣ ሁሉን ብነግርሽ ልትሸከሚው አትችዪምና እባክሽ በቃሉ ታማኞች እንድንሆንና ቃሉን በትጋት የሚያስተምሩንን እግዚአብሔር እንዲያስነሳ ጸልዪልን።
ሉሊትዬ የኔ ብሶት ማቆምያም የለውም ባይሆን ሌላውን ደግሞ በሌላ ደብዳቤ ብገልጽልሽ ሳይሻል አይቀርም። እኔም ዓይኖቼ እንደመደብዘዝ ሲላቸው ይታወቀኛል። በአካባቢያችን የኮሽታ ድምጽ እንኩዋን አይሰማም። ፍጥረትም በውድቅት ሌሊት አሸልቧል። ትንሿ አልጋዬም “አይበቃህም እንዴ” ብላ ድምጽ አውጥታ የምትጣራ ይመስላል። ወደዛው ልሂድ።
አንቺ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርቺ። በጊዜውም ያለ ጊዜውም በመጽናት ጌታን አገልግዪው። ጌታ በሰጠሽ በዚህ ቀን ፈቃዱን እንድታገለግይና በጸሎት እንድትጋደዪ እጸልያለሁ። ቀድሞ የነበረሽ በጎ ህሊናና የንጽሕና ሕይወት አይወሰድብሽ። “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር፣ የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነሽ የተፈተነውን ራስሽን ለእግዚአብሔር ልታቀርቢ ትጊ”

የኮልፌ ወጣቶች ሰላም ብለውሻል

የክርስቶስ የሆነው ተሻገር

One comment

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *