እንዴት ብለን እንመልሳቸው? – ኮነ ፍሥሐ

እንዴት ብለን እንመልሳቸው? – ኮነ ፍሥሐ

አብሮኝ የሚያገለግለው ወንድም እራሱን እና የሚያገለግልበትን ድርጅት ወደ ውድቀትና ተጠያቂነት ውስጥ የሚወስድ ድርጊት ሲፈጽም ማየት ከጀመርኩ ሰነበትኩ። ተው ጥሩ አይደለም ከማለት ያለፈ ጠንከር ያለ ምክርና ተግሳጽ ለመስጠት ፍርሃት ይዞኛል። ምናልባትም ከአሁን በፊት ሰዎችን ያለእውቀት ለመገሰጽ ያደረግሁት ሙከራ የፍርሃት ጠባሳ ጥሎብኝ ያለፈ ይመስላል። እንደ ሰጎን እራሴን አሸዋ ውስጥ ቀብሬ ስህተቱንም ጥፋቱንም አላየሁም እያልኩ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በግለሰቡም ሆነ በድርጅቱ ውድቀት እኔም ተወቃሽ እንደምሆን ጥያቄ የለውም። ምንአገባኝ የሚለው ከመሪነት የሚያሸሽ አባዜ እንደ ብዙዎቹ ደካማ መሪዎች የተጠናወተኝ ይመስላል። ይህ የእኔ ብቻ ችግር አይመስለኝም። በዙርያዬ ያለ ሁሉ አይቶ እንዳላየ መሆንን መርጧል።

ታድያ ለምንድነው አይቶ እንዳላየ የምሆነው? ለምንድነው የምናየውን ስህተት ለመናገር የምንፈራው? ህሊናችን ተናገረው፤ የእግዚአብሄር ቃልም፣ መንፈስ ቅዱስም ስህተት መሆኑን ሲነግረንና ተመለስ በለው፣ መቀየር አለብህ በለው፣ ስህተት እንደሆነ ንገረው! እያለ ሲወቅሰን ለምንድነው እኛ ዝም የምንለው። አዎን ምክንያቱ “ሰውን ለመገሰጽ ፍርሃት” ይባላል። አዎን ሰውን መገሰጽ ዋጋ ያስከፍላል። በተለይ ግሳፄ ሰውን የተቆለለ ማንነቱን ስለሚነካ በተለይ በዝና የተካቡ ሰዎችን ለመንካት አስቸጋሪ መንገድ ነው። በጅምላ ስናየው የእኛ ፍርሃትና ያለመታዘዝ ለሌሎች የውድቀት ምክንያት ዋናው ነው።

ምንድነው የምንፈራው? እንዴ አትፍራ፣ አትፍራ! አትፍራ! አትፍራ!! ተብሎ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጽፎልን የለም እንዴ? አዎን የምንፈራው ብዙ ነገር አለ። አሁንማ የወደፊት ታሪካችን ሲጻፍ “የፈሪ ትውልድ” ሳንባል አንቀርም። በተለይ ተመለስ፡ ተስተካከል፡ ልክ አይደለህም! ከሚባለው ታራሚ ዘንድ የሚወጣ ትልቅ ቁጣና ተቃውሞ እጅግ ያስፈራናል። በሰዎች ዘንድ ለጊዜው አለመወደድ አለ። ጥቅም እና ግብዣም ሊቀር ይችላል። እንደ ታራሚው ደጋፊ ወይም አራጋቢ ብዛትም ይለያያል። አንዳንዴ ቁጣውና ተቃውሞው ከታራሚው ሳይሆን ከጭፍን ደጋፊዎችም ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን የእኛ ፍርሃትና እርማቱን ለመናገር አቀራረባችን ወሳኝነት አለው።

ለመገሰጽ  ዋና ጠቃሚ ምክር ፦ የመሪነት ብቃትን ማዳበር

ጥሩ መሪ ከሚታወቅበት ዋና ባህርይ አንዱ ለችግሮች ሁሉ እራሱ መፍትሔ የሚያመጣ ሳይሆን፡ ችግሩን ቶሎ ተመልክቶ፣ ለችግሩ መፍትሔን ከሚመራቸው ውስጥ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው። ይህንንም ለመተግበር ጥሩ መሪዎች የሚመሩትን ሕብረት እንዳይበላሽ እየጠበቁ የሚመሩትን ሕብረት የማይመች እውነታዎችን እንዲጋፈጥ ያደርጋሉ:: በዚህም የሚመሩትን ሕብረት ወይም ግለሰብ ከእግዚአብሔር እውነታ ጋር እያጋጩ ግለሰቡ ወይም ሕብረቱ እውነታውን ተረድቶ ለችግሩ እራሱ መፍትሔ እንዲያመጣ ያደርጉታል። ይህ የብዙ የተመሰከረላቸው የመንፈሳዊ መሪዎች ባህርይ ነው። የሚመሩህ ቃል አሰምተው አንተን ሊያስተገብሩህ፤ እንዲሁም እራስህን በእግዚአብሔር ቃል መስታወት ውስጥ እያየህ እንድትስተካከል እንጂ ሊያስተካክሉህ አይደለም። ያዕቆብ 1:23 “ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ 24 ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።”

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ጥሩ የቤተ እምነት ወይም የአገልግሎት መሪ የሚመራው ሕብረት ዝም ብሎ የሚከተለው ጀሌ ሳይሆን፤ ተመሪው እራሱን በእግዚአብሔር ቃል እየመረመረ እውነትን ለመናገር ድፍረት ያለውና ለመስተካከልም ፈቃደኛ ልብ ያለው መሆን አለበት። ዛሬ ጊዜ ብዙ መሪዎች ጥያቄ ሳያነሳ ዝም ብሎ የሚመራ ተከታይ ማፍራት ላይ ሲደክሙ ይታያሉ። ስህተትን መናገር ሕብረትን ያፈርሳል በሚል የተሳሳተ የአመራር ዘይቤ በተከታዮች ወይም ምዕመኖች መሃከል ሊያድግ የሚገባውን የመምከር፡ መመካከርና ስህተትን የመገሰጽ ጸጋ ያዳፍኑታል።

ዝም ብሎ ያለ ጥያቄ የሚመራ ሕብረት ካያችሁ መሪዎች ተጠንቀቁ። እንደ ጥሩ ነገርም አትመልከቱት። ለመናገር፤ ለመምከርና ስህተትን ስህተት ካልኩ እገለላለሁ ወይም እጠላለሁ ብሎ የሚፈራ ሕብረት ከሆነ ሊደርስ የሚችለው አሳዛኝ አደጋ “ንጉሱ ልብስ የለውም” የሚባለው የህፃናት መጽሐፍ ትረካን ይመስላል።

ታሪኩ እንዲህ ነው፦ “ንጉሡ ከማንም ምክር የማይቀበልና ጸጥ ለጥ አድርጎ ገዢ ነው። ለንግሥ ክብረ በዓል ቀኑም የሚለብሰው ልዩ የሆነ ልብስ ፈለገ። ይህን የሰማ አንድ ተንኮለኛ ልብስ ሰፊም ይህንን ግብዝ ንጉሥ እጅግ የተለየ ልብስ እንደሚሰፋለት እንዲህ በማለት አሳመነው፦ “ እኔ የምሰፋልህን ልብስ ለብሰህ ማየት የሚችሉት እጅግ በጣም ታማኝ፤ ጎበዝ እና የተወደዱ ተከታዮችህ ብቻ ናቸው።” አለው። ይህም ልብስ ሰፊ ንጉሡን በዚህ የተንኮል ሃሳብ አሳምኖት በክብረ በዓሉ ላይ እራቁቱን “ልዩ ልብስ ለብሻለሁ” ብሎ በሰገነቱ ላይ እንዲቆም አደረገው። ስለ ንጉሡ ልዩ ልብስ የተነገራቸው የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉ ልብስ ያልለበሰው ንጉሥ ፊት እየቀረቡ እጅ በመንሳት ልብሱን ማድነቅ ጀመሩ። የሚገርመው እርስ በርሳቸውም ስለ ንጉሡ ልዩ ልብስ በማድነቅ ማውራታቸው ነበር። ንጉሡም ከብዙ ባለሙዋሎቹ በሰማው ምስክርነት የተነሳ ልዩ ልብስ ለብሻለሁ ብሎ በኩራት ተንጎራደደ። ልብ በሉ….. የቆመው ግን እራቁቱን ነው። በበዓሉ መጨረሻ ሰዓት ላይ ወደ ንጉሡ የቀረበ አንድ ህፃን ግን ንጉሡን ሲያይ ደንግጦ የንጉሡን እራቁትነት ደፍሮ እየደጋገመ ተናገረ። ይህም ንጉሡን እንዲጠራጠርና እራቁትነቱን እንዲያውቅ አደረገው። ሆኖም ይህ እውነታ የታወቀው ንጉሡ ለሰዓታት ያህል በታላቅ መድረክ ላይ እራቁቱን በብዙ ህዝብ ፊት ከቆመ በሁዋላ ነበር።

እንግዲህ ጸጥ ለጥ አድረገው የሚያስተዳድሩ ይህን መሳይ መሪዎች በመሃከላችን ብዙዎች ናቸው። አንዳንድ ጊዜም የሌላቸውን ጸጋ ለብሰናል እያሉ በመድረክ ላይ ሲፋንኑ ዝም የምንልበትም ምክንያቱ የራቁታሙን ንጉሥ ታሪክ ይመስላል። ብዙዎች እሲኪጠፉና እስኪወድቁ ድረስ የዘገየንበት ምክንያትም ይህ ነው። ለዚህ ነው የመሪነት ብቃት አለመኖር በመሃከላችን ሊኖር ለሚገባው የምክክር እና የመወቃቀስ መጥፋት ከፍርሃት ቀጥሎ ምክንያት የሆነው።

እባካችሁ ስህተት አደባባይ መድረክ ላይ እስኪወጣ አንጠብቅ። ለመምከር እና እውነትን በመናገር ለመገሰጽ እንድፈር። እስቲ ለምንድነው ለመገሰጽና የተሳሳቱ ወንድሞች፣ እህቶች ወይም አገልጋዮች ወደ ታላቅ ውድቀት ሲያመሩ እንዲመለሱ ለመናገር የምንፈራው?

 1. የአየነውን እንጠራጠራለን። አይናችንንም አንዳንዴ “ ዐይኔ ነው” በማለት እንጠራጠረዋለን።
 2. ምን አልባት ስህተቱ ከኔ ይሆን በማለት እንጨነቃለን።
 3. የሰው ጉዳይ ውስጥ ለምን ጣልቃ ገብቼ አበላሻለሁ። እኔ ምን አገባኝ የሚሉት ናቸው።

እንግዲህ ጥሩ የቤተሰብ፣ የቤተክርስትያን ወይም የማሕበረ ሰብ መሪ ከእነዚህ ፍርሃቶች በላይ ሆኖ ለመምከርና ለመገሰጽ ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል።

እስቲ ለመገሰጽ የሚረዱ ጥቂት ጠቃሚ ምክሮችን በመጀመርያ እንካፈል። ምክንያቱም አንዱ ችግራችን እንዴት እንደምንገስጽ ስለማናውቅ ይመስለኛል።

 1. በፀሎት ወደ እግዚአብሔር ቀርበህ መመርያን ጠይቅ፦በተለይ ይህንን የምታደርገው ለወንድምህ ካለህ ፍጹም ፍቅር እንጂ የራስህን አጀንዳ ለማሳካት አለመሆኑን አረጋግጥ። ለዚህም የመጀመርያው ማረጋገጫ ወንድምህን ስህተቱን ለብቻው ሌላ ሰው ሳይሰማ ስትነግረው ነው። (ማቴ 8: 16 )
 2. አትፍጠን ወይም አትዘግይ፦ ስትፈጥን ነገሩን በደንብ ካለመገንዘብ የተነሳ ሰውን ልትጎዳ ትችላለህ። ኤሊ የምታለቅሰውን ሴት ሰከረች ብሎ እንደገሰጸው ማለት ነው። ስትዘገይ ደግሞ ከፍርድ በሁዋላ ትደርሳለህ። ያው ኤሊ ወንድ ልጆቹን በሰዓቱ ባለመገሰጹ ሲቀሰፉ እንዳየነው ማለት ነው። በተለይ ሰዎች በስህተታቸው ወደ ሞት ሲሄዱ አትዘግይ። አለዝያም ቢቢሲ እና ቪኦኤ ሲያወሩት በድንገት ትሰማና እርምጃ በጊዜው ባለመውሰድህ ወይኔ ይህን ባደርግ ኖሮ እያልክ ትጸጸታለህ።

በተለይ የቤተክርስትያን ህብረትንና አስተምህሮን የሚያዛንፉ ክስተቶች ሲከሰቱ መዘዛቸው አደገኛ ስለሚሆን አለመዘግየት ተገቢ ነው።

 1. ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እነዚህን አምስት ስህተትን የመናገርያ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ መንገዶች አጥና ።

  • እግዚአብሔር እዮብን በብዙ ጥያቄ (በተዘዋዋሪ መንገድ)፡ አላዋቂነቱን ተገንዝቦ ንስሃ እንዲገባ አደረገው። እዮብ 38:2፤ ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? ፤ እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። 4፤ ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?
  • ጌታ እየሱስ ፈሪሳውያንን በወይኑ እርሻ ምሳሌ(PARABLE) ሉቃስ 20: 9 _19 (በተዘዋዋሪ መንገድ) ጌታም ምሳሌውን ለካህናት አለቆች ጻፎችና ሽማግሌዎች ነግሮ ሲያበቃ “ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ።”
  • ናታን ዳዊትን፡ እውነተኛና ተመሳሳይ ታሪክ በመንገር “ያ ሰው አንተ ነህ” በማለት ወደ ንስሃ አመጣው 2ተኛ ሳሙኤል 12:1:3(በተዘዋዋሪ መንገድ)
  • በቀጥታ ሰዎች ለማየት የታወሩበትን አይምሮ መናገር።(ቀጥተኛ ግሳፄ) ጌታ እየሱስ “ከእናንተ ሃጥያት የሌለበት የመጀመርያውን ድንጋይ አንስቶ ይውገራት”(የኋ 8:7) ብሎ ሲል በዚያ የተሰበሰቡትን ሴቲቱን ጨምሮ በሃጥያታቸው እንዲወቀሱ አደረገ። እርሷንም ዳግመኛ ሃጥያትን አትስሪ ብሎ አሰናበታት። ሃጥያት ሲደጋገም አእምሮአችንን በማደንዘዝ ለመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ የማንታዘዝ ያደርጋል። በዚህም ጊዜ እግዚአብሄር ለታወረው አይምሮአችን በቀጥታ በመናገር የሚመልሱን ሰዎችን ይልካል።
  • በቀጥታ ያለማመንታት ስህተቱን ወድያው በመናገር እንዲታረሙ መገሰጽ። ይህንን በሉቃስ 23:40 ላይ ከጌታ ጋር የተሰቀለው ወንበዴ ሌላውን ወንበዴ “እግዚአብሄርን አትፈራም” በማለት ሲገስጸው እንመለከታለን። እንዲሁም ጌታ ጴጥሮስን “ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤” (ማር 8:33) ብሎ ገስጾታል። ሆኖም ይህ መንገድ ጥንቃቄ እና ለውጥ ለማምጣት ቀጣይ ክትትል ያስፈልገዋል።
 2. ለምትመክረው ወይም ለምትገስጸው ሰው ስሜቱን እንዲገልጽ ፍቀደለት።

ተወቃሹ በደልና ስህተቱን ስትነግረው ሊያለቅስ፣ ሊያዝን ወይም ሊቆጣ ይችል ይሆናል። አንተ ግን ከቦታህ አትንሸራተት። ዓላማህ በፍቅር ወንድምህን መመለስ መሆኑን በፍጹም አትርሳ፣ ይህንንም ፍቅርህን ከመግለጽ ወደ ሁዋላ አትበል። አትፍራ! አሁን ቅድመ ዝግጅትህን ጨርሰህ የመሪነት ብቃትህ የሚለካበት ቦታ ላይ ነህ።

 1. ይህንን በማድረግህ እግዚአብሔር የሚከብርበትን ምክንያት በጽሑፍ ዘርዝረህ ያዝ። ይህም ከያዝከው ግብ ለመድረስ መመርያ ይሆንሃል። ለምሳሌ ፦ ወንድሜ ኑሮው፣ትዳሩ፣ ልጆቹ እና አገልግሎቱ ይባረካል። ከሚመጣው ፍርድ ይጠበቃል። ለሌሎች ምሳሌ በመሆን እግዚአብሔር ይጠቀምበታል። መልካም ምስክርነት ይኖረዋል። እግዚአብሔር ነገሩን እያየው ነው የሚሉና የመሳሰሉት ናቸው።
 2. የእግዚአብሔርን ፍቅር:ታጋሽነት እና ይቅር ባይነት አትርሳ።

እንግዲህ በክርስቶስ አካል ውስጥ ጠቃሚ ሆነን ለመመላለስ የሌሎች የስህተትና የበደል አካሄድ ግድ ሊለን ይገባል። እኔ ምን አገባኝ፣ ይቅር ብዬው ዝም ብዬ ለምን አልሄድም? የሚለው የብዙዎች የፍርሃት መንገድ ጠቃሚነቱ ለራስ እንጂ አካሉን አያንጽም። ለሌሎች ግድ ሊለን ይገባል። የሚበድሉ የሚሳሳቱ ሰዎችን ለመመለስ ጥቅስ ከመወርወር ባለፈ ምክር ለመመለስ እና ቸል በማለት የተተወ በደል ስር እንዳይሰድ ቤተክርስትያን ይቅርታን ብቻ ሳይሆን በዳይን መገሰጽና መመለስን ልታስተምር እና የደቀመዘምራን ክህሎት ልታደርገው ይገባል።

ጸሐፊው ኮነ ፍሥሐ- በሃገረ አሜሪካ በቨርጂንያ ክፍለ ግዛት የወንጌል አስተማሪና የሥነ ጽሁፍ ስው ሲሆን በአሜሪካን በአውሮፓ እና በደቡብ አፍሪካ የሚሰራጨው የ”ባለጸጋ ክርስትያን” መጽሔት ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የ”እውነት ቀንዲል” መጽሔት ተ/አዘጋጅ ነው። ለክርስትያኖች የሚያዘጋጀውን ትምህርትና የስነ ጽሁፍ ስራዎቹን ለመመልከት WWW.Baletsega.com እና www.Tsega.com ድረ ገጾችን ይመልከቱ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *