ገደብ አለው – የሕይወት መስታወት

ገደብ አለው – የሕይወት መስታወት

ቸኮል ጌታን እንደ ግል መድኅኒቱ አድርጎ የተቀበለው ገና በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ሆኖ ነው። ለጌታ ካለው ፍቅር የተነሳ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ወሰነ። መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሮ ሲጨርስ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስትያን የወጣቶች ፕሮግራም ላይ ማገልገል ጀመረ። ለተወሰነ ጊዜም በአገልግሎቱ ውስጥ በሁሉም ነገር ተደስቶ ያገለግል ነበር:: ይሁን እንጂ፥ በቤተክርስትያን ውስጥ በተነሳው ግጭት ምክንያት ቤተክርስትያኑ ለሁለት ሲከፈል አዝኖ አገልግሎቱን አቅዋርጦ ቤትና መኪና የማሻሻጥ ስራ ውስጥ ገባ። ባለው ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታው ተጠቅሞ በአጭርጊዜ ውስጥ በስራው ከፍተኛ ውጤት አገኘ። ብዙ ገንዘብም ለማጠራቀምና ለመያዝ ቻለ። አዲስ መኖርያ ቤት፣አዲስና ውድ መኪናም ገዛ።በአጠቃላይ በኑሮው በጣም የተደላደለ ሆነ።
ዘወትር የሚገኝበት አካባቢ፣አብሮ የሚውላቸው ሰዎች ሁሉ ተለወጡ። ጓደኞቹም ዓለማውያን ኅብታም ነጋዴዎች ሆኑ። መንፈሳዊ ሕይወቱም ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ መጣ። ቤተክርስትያን ከሚሄድበት የማይኄድበት ጊዜ እየበለጠ መጣ። አዲስ ያፈራቸውን ጉዋደኞች ለመምሰልና ለማስደሰት ሲል መጠጥ ቤት መሄድ እና ቀስ በቀስም የሚያሰክር መጠጥ መጠጣት ጀመረ። የሚናገረው ቋንቋ ሁሉ እየተለወጠ መጣ። ክርስትያን በነበረበት ወቅት የማያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ምንም ዓይነት የህሊና ወቀሳ ሳይሰማው ማድረግ ጀመረ። በመጨረሻም ከቤተ ክርስትያን አንደኛውን ቀረ። መንገድ ላይ ክርስትያኖችን ሲያይ ፊቱን አዙሮ አቅጣጫ ቀይሮ ይሄዳል።
ቸኮል ለአጭር ጊዜ ያወቃትን ሴት አገባ ። በዓመት ጊዜ ውስጥ እርስዋን ፈቶ ሌላዋን አገባ። ሁለተኛዋን ሚስቱንም የስድስት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆነች ፈታት። አራት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ሁለት ሚስት አግብቶ ሁለቱንም ፈታ። የተወለደውንም ልጁን አንድም ቀን እንኩዋን አላየውም። ቸኮል በዓለም ውስጥ የተሳካለት ይምሰል እንጂ፥ ፍጹም ደስተኛ ሰው አልነበረም።
በዙርያችን ብዙ ቸኮልን የሚመስሉ እግዚአብሔር ከወሰነላቸው ድንበር(ክልል) ቀስ እያሉ በመውጣታቸው ከፍተኛ መላላጥ በህይወታቸው የደረሰባቸው ሰዎች በየጊዜው ያጋጥሙናል። ጌታ ኢየሱስ በምሳሌ የተናገረው ኮብላዩ ልጅ፣ በአባቱ ቤት ጥሩ ኑሮ ቢኖርም፣ ከዚያ የበለጠ ደስታ በመፈለግ ከአባቱ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ መኖርን ፈለገ(ሉቃ 15)። ፈቃዱን መጫን የማይፈልገው አባት፣ የጠየቀውን ሁሉ ሰጥቶ ልቡ እያዘነ አሰናበተው። ድንበር ጥሶ ሄዶ ደስ ያለውን ሁሉ ማድረግ ጀመረ። ይሁን እንጂ፥ “አባቴ ካበጀልኝ ክልል ወጥቼ በረሃብ መሞቴ ነው” ብሎ በማሰብና በመጸጸት ተመልሶ ወደ አባቱ ጉያ ገባ። በእግዚአብሔር ፈቃድ ሥር መኖር ለጊዜው መንገዱ ጠባብና አስቸጋሪ ይሁን እንጂ፥ ያ የሕይወት መንገድ ስለሆነ፣አስቸጋሪም ቢሆን እርሱ ይሻለናል።
ከእስራትና ከሀፍረት ሕይወት ራሳችንን ለመጠበቅ እንድንችል ፣የምንወዳቸው ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊጎትቱና ከጌታ ሊያስወጡን ይችላሉ ብለን የምናስባቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ እንወቅ። ከጌታ ጋር ካለን ግንኙነት የበለጠ በሕይወታችን የምናስቀድመው ነገር ይኖር ይሆን? በግድ የለሽነት ወይንም በተለያዩ ነገሮች በመጎተት ጌታ ካበጀልን ቅጥር በመውጣት በሕይወታችን ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስብን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።
እግዚአብሔር በአበጀልን ክልል ውስጥ ለመኖር፣ ከዚህ በፊት ያፈረስናቸውን ክልሎች (አጥሮች) እንደገና እንስራቸው። አጥር የቤት እንስሳትን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳል። ከብቶች ብቻ ሳይሆኑ ሰውም የትም እንዳይባክንና እንዳይጎዳ ክልል(አጥር) ማበጀት ይጠቅመዋል። ክርስትያን ከድንበር እንዳይወጣ የሚጠብቁት ክርስትያናዊ ልምምዶች አሉት። በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ፣መጸለይ፣ከክርስትያኖች ጋር ሕብረት መፍጠር ድንበሩን ጥሶ እንዳይሄድ ከሚጠብቁት ዋናዎቹ ናቸው። ከክልሉ ውጪ ወጥቶ ከሆነ፣ እነዚህን ያፈረሳቸውን ክልሎች እንደገና ቀስ በቀስ ማበጀት ይኖርበታል።
የእግዚአብሔርን ቃል ስናጠና ገደቡን ቀስ በቀስ ከጥቃቅን በመጀመር እየደጋገመ የጣሰውን ሳምሶንን እናያለን። ይህን ሲያደርግ በራሱ ኅይልና ጉልበት ተማምኖ እንደሆነ ግልጽ ነው። እኛስ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥመን ውስጣዊ ትግል ምን ዓይነት ይሆን? ጊዜያዊ ደስታን በመፈለግ የተሰጠንን ገደብ ጥሰን እየሄድን ይሆን? ገንዘብ፣ ሥልጣንና ዝናን ለማግኘት እግዚአብሔር የማይወደውና የማይደግፈውን ነገር እያደረግን ይሆን? በራሳቸው ኀይልና ችሎታ የሚተማመኑ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ጊዜ የተሰጣቸውን ክልል ወይም ገደብ ችላ ይላሉ። ይህንን በማድረጋቸውም ራሳቸውን ትልቅ አደጋ ላይ የጣሉ ናቸው። እኔና እናንተ የተሰጠንን ክልል ወይም ገደብ ጥሰን ስንሄድ፣ እንደ ሳምሶን ብርሃናችንን ልናጣ፣በሰንሰለት ተጠፍረን ልንታሰርና ለጠላት እህል ፈጪ ሆነን ልንዋረድ ስለምንችል እንጠንቀቅ።
ሰይጣን ሌሎችን ባጠመደበት ወጥመድ እንዳያጠምደንና እንዳይጥለን ነቅተን እንጠብቀው። ለእኔነታችንም ገደብ እናብጅለት!
ጌታ ይባርካችሁ!

One comment

  1. Menbere Tenkir says:

    God bless you. It sounds very familiar. Thank you Lord Jesus! Your love drew me back to my right mind and helped me lean on you in times of distress and life challenges. You are the stronge tower I run into. Awsome reminder for me personally and I am sure many will relate to this story. Thank you so much for your ministry.moo

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *