ፈለጋቸውን እንከተል – ሰሊሆም መጽሔት

ፈለጋቸውን እንከተል – ሰሊሆም መጽሔት

ስለ ማሄ ስለ ደፈርሻ፣ዳንጎ፣ ናና፣ ላሊሳ፣ ተካ፣ አኒሳ ስለነ ጎዎታ ሌሎችም በወላኢታ ሃድያ በጸሃያማው ስፍራ በበረሃው ቦታ በአባይ በረሃ በጎሙዝ ስለወንጌል የተከፈለውን ዋጋ እንዳልተርክ አቅም አጣሁ፣ ስቃያቸውን መከራቸውን በሞት ሸለቆ እየሄዱ ጌታን መናፈቃቸው እንደ ጌታቸው በደም ጣር ሆነው ስለሚያሰቃይዋቸው ሰዎች መጸለይና መማለዳቸውን ሳስብ ይገርመኛል።
ረጅም መንገድ ተጉዘው አራዊት ባሉበት ጨለማ ቦታ አናብስት፣ ነብር፣ ዘንዶ ባጠገባቸው እያለፉ ሳይፈሩ ነብሳቸውን ሊያገለግሉት ለወጡለት አምላካቸው አደራ ሰጥተው በዝምታ ያልፋሉ። ከቤታቸው ሲወጡ ዓላማ አድርገው የተነሱበትን የነብሳትን መዳን ቅዱስ ተግባር አልረሱም።
ያልዳነ እንዳይኖር መመርያቸው ነበር። ጨለማ፣ ምሽት፣ ክረምትና በጋ፣ ረሃብ፣ ጥማት፣ ሐዘን፣ተስፋ መቁረጥ ሳይበግራቸው ለወንጌል ይዘምቱ ነበር። የወንድማቸው ሬሳ በተቃዋሚዎች ተገድሎ፣ ሬሳው በደም ተጨማልቆ ፣ በጦር ተወግቶ በቆንጨራ የተቆራረጠውን አካል እያዩ ነግ በእኔ ብለው አልፈሩም። እየዘመሩ ጀግና የእምነት ወንድማቸው በመከራው ባጋጠመው ነገር ሳይበገር በእምነቱ እንደጸና አንቀላፋ፣ “ነገ በሰማይ ከቅዱሳን ጋር እናገኘዋለን” በማለት፣ እስከዚያው ድረስ የተጀመረውን የወንጌል ጉዳይ ለነብሳት ለማድረስ አደራውን ተቀብለው ለመፈጸም ልባቸውን አጠንክረውና ወገባቸውን አስረው ወደ ፊት ይቀጥላሉ። ከሄዱበት ሲመለሱ በመንገድ ላይ የቀበሩትን የወንድማቸው ሬሳ ያረፈበትን መቃብር እያዩ ወገናቸውን በጭካኔ ለገደሉባቸው ሕዝብ በመቃብሩ አጠገብ በርከክ ብለው ይጸልያሉ፡ ጌታ ሆይ ይቅርበላቸው ያደረጉትን አያውቁምና አትዘንባቸው ይልቅስ የፈሰሰው የወንድማቸው ደሙ ለመዳናቸው ምክንያት ይሁንላቸው ብለው ይጸልዩና ፀሃይ ሳትጠልቅባቸው ወደ ሌላ ቦታ ወንጌል ለማድረስ ጉዞ ይጀምራሉ።
ወዴት ትሄዳላችሁ? የሚል ጠያቂ ቢያጋጥማቸው መልሳቸው “የምስራቹን ቃል ላልደረሳቸው ህዝብ ለማድረስ” ይላሉ። አትፈሩም ወይ? ቢባሉ መልሳቸው አንድ ነው። እኛ “ ሃጥያትን ላለማድረግ እንጂ ሞትን አንፈራም” ይላሉ በፈገግታ። ያመኑትን ያውቃሉ፣ የታመኑለትም ጌታ እንደማይተዋቸው አምነዋልና ዋጋቸውን ተምነው ይወጣሉ።
ይህ 400 ኪሎ ሜትር ዕርዝመት ያለውን የስምጥ ሽለቆ ለሁለት ከፍሎ በሚሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌልን የዘሩት የኢትዮጵያውያን የወንጌል ሰማዕታት እና የዕምነት አርበኞች ታሪክ ነው:: የእነኚህ ሰማዕታት ደም የወንጌል ዘር ሆኖ የዛሬውን ትውልድ አብቅሏል። በዚህ የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍል እግዚአብሔር በሐዋርያት ስራ ውስጥ ከተፈጸመው በላይ ከፍ ያለ ተዓምር እንደፈጸመ ብዙ ጸሓፊዎችና በመከራው ውስጥ ያበቡት ከሶስት ሺህ በላይ አጥቢያዎች ምስክሮች ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች “ እግዚአብሔር በሰው መሃከል ወረደ” እስከማለት ድረስ ህዝቡን አስደንቀዋል።
ይህ ታሪክ ለመኩራራት ሳይሆን ስላለፈው ምስጋና በመስጠት ከታሪክ ጠቃሽነት ባለፈ መልኩ ታሪክን የሚሰራው ጌታን በዘመናችን እንዲሰራ በመጋበዝ እንድንነቃቃና ዛሬም በትውልድ ተራችን የእግዚአብሄርን ወንጌል አደራ ተቀብለን ለምንሮጥ ለእኛ እየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሮጥ ዘንድ የሚያበረታታን ይሆናል::
ልብ በሉ “የዛሬ መሰረት ትናንት ነው! የነገ መሰረት ደግሞ ዛሬ ነው! የትናንት፡የዛሬና የነገ ባለቤት እግዚአብሔር ነው:።” ወንጌል ክቡር ነገር ነው፣ ወንጌል ቸል የሚባል ጉዳይ አይደለም፣ልናቀለው አይገባም፣ ለምን ቢባል በብዙ ዋጋ የተከፈለ በደም መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ጉዳይ ነውና። በዚህ ዘመን ያለ ትውልድ ከመዝለልና ከመዘመር ያለፈ የእምነት አባቶች አደራ አለበት። ደማቸውን አፍስሰው መከራን ያለልክ ከፍለውበታልና፡ ስለዚህ የቃላቸው፣የመከራቸውና የስቃያቸው የአደራ ቃል አለበት። ዛሬ ያለችውን ቤተክርስትያን ያቆዩዋት የቀድሞዎቹ ክርስትያኖች የከፈሉትን ዋጋ መርሳት አይገባንም።
ዛሬ ሌላ ዋጋ የሚያስከፍል ዋጋ ልንከፍልበት የምንጠየቅባት ዘመንና ዓመት ላይ ደርሰናል፣ ወንጌል የተረት ተረት ጉዳይ አይደለም። የአባቶች የወንጌል ገድል በእኛ ዘመን ይደገም ዘንድ ግድ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ የነበሩት ቀደምት የወንጌል አባቶች በዘመናቸው የተሰጣቸውን ያመኑትን የወንጌል አደራ ሰርተውና ፈጽመው አለፉ። ዛሬ ተራው የኛ ነው፣ የሁላችን ነው። እስከ ሞት የታመንህ ሁን የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ። የተጠራንለት ለዚህ ነውና፡ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሎአልና። 1ኛ ጴጥ 2: 21
ይህ ጽሁፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ሆነው ወንጌልን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ስላስፋፉት ቀደምት ሰማእታት በወንድዬ ዓሊ ከተጻፈው የእኩለ ሌሊት ወገግታ ከሚለው ጽሑፍ ለሚቀርበው ዝግጅታችን መንደርደርያ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት “ከመቃብር የወጣው ሰባኪ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ተከታይ ጽሑፍ ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *