“እንባዬን ተዉልኝ” ከሰለሞን አበበ

“እንባዬን ተዉልኝ” ከሰለሞን አበበ

“ልባችን ጥያቄ ማንሣትና ማልቀስ በቻለ ጊዜ አንዳች የግንዛቤ ብርሃን እናገኛለን። … ግፉአን ያለቅሳሉ፣ የተናቁና ግልምጫ የጠገቡ ሞንዱባን ያለቅሳሉ፣ የተጣሉ ያለቅሳሉ፤ … ቢያንስም ቢያድግም፣ በተመቻቸ ኑሮ ውስጥ የምንኖር ሰዎች ግን፣ እንዴት ማልቀስ እንደምንችል ማወቅ ተስኖናል። አንዳንድ የሕይወት እውነተኛ ገጽታዎች መታየት የሚችሉት በእንባ ታጥበው በነጹ ዐይኖች ብቻ ነው።”
ይህችን ጹሑፍ የምጫጭረው ስለ እንባ የምለው ኖሮኝ ነው ።“እንባዬን ተዉልኝ” እል ዘንድ ለዛሬ ተገደድሁ። ወገኖች ሆይ፣ አንዳንድ ጊዜ አልቅሱ አልቅሱ አይላችሁም? የተትረፈረፈ የእንባ ምንጭ አይናፍቃችሁም (ኤር. 9፥1፤ 14፥17፤ ሰቈ. )?
የምን እንባ ነው የምታወራው ካልተባልሁ ነው እንግዲህ። “የሣቅ ነው ዘመኑ” በተባለበት ልቅሶን ምን አመጣው? ዐውቃለሁ፤ አንዳንድ አንባቢዎች “ውይ፣ ሲያሳዝን … ያልገባው ምስኪን … ዝም ብሎ ያለቅሳል” ማለታቸው አይቀርም። “የከፍታ ዘመን”፣ “የመስፋፋት ዓመት”፣ “የጥርመሳ ጊዜ”፣ “የማለፍና የመብረር ቀናት”፣ “የእልልታ ዘመን”፣ “የብዝበዛ ዓመት”፣ “የመውረስና የመሻገር ዓመት”፣ “የሞገስና የቅባት ዘመን” ወዘተ. እየተባለ በተነገረበትና በሚነገርበት አፍላ እብደት ውስጥ እናልቅስ ብሎ ነገር ምን ይሉት ቀፋፊ ንግርት ነው?
ግና ለምን አናለቅስ? በኾነልንና ባለቀስን፤ ጨምረንም ባነባን እላለሁ። እውነት በአደባባይ ሲወድቅ፣ ለምልሞ የታየው ምሽት ላይ ሲደርቅ የእንባ ማድጋ እንሰብራለን። በበጎች መስክ ተኵላ ሲርመሰመስ፣ ግርግሩ በዝቶ ነውር ባናት ሲፈስ አመድ እንነሰንሳለን። ዘመን ከፍቶ ቃሉ ሲደፈር፣ ጻድቅ ቀን በሰጠው አባጭ ሲሰበር፣ አምልኮተ እግዚአብሔር ድል ባለ የዳንኪራ መንጦልጦል ሲተካ መሣቅ ይገኝ አይመስለኝም። ድኾች ሲነቀሉ፣ መሪዎች ሲበድሉ፣ ባለጠጎች ሲፏልሉ፣ ለሐቅ የቆሙ ሲገለሉ … እንባ ማፍሰስ ቢያንሰን እንጅ ለምን አይባልም። ፍርድ ሲዛባ፣ ግፍ ሲገነባ፣ ስንፍና ሲናኝ፣ ትጋት ሲናናቅ እንዴት ዝም ይባላል? “ዓይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ የዓይናችንም ሽፋሽፍቶች ውሃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ይያዙ” (ኤር. 9፥18)።
ቀለብ የሚዛቅበት እስከ ኾነ ድረስ መንገደኛው ሁሉ ከነ ኑፋቄው የቅዱሳንን ጉባኤ ሲወር አይተክዙም? ትዳር ሲፈርስ፣ ቤት ሲታመስ፣ ሕፃናት ጎዳና ወጥተው ሲበተኑ አይቃትቱም? መበለቶች ሲገፉ፣ ደኻ አደጎች ሲሰናከሉ ልብ መች ዝም ይላል? የማኅበረ ሰቡን ድጋፍ የሚጠባበቁ ድኵማን ሲዘረፉ ምላሻችን ምን ይኹን? ቀዳሚ ባለውለተኞች ከታሪክ መዝገብ ሲፋቁ አይጐመዝዝም? አረጋውያን ሽበታቸው ሲደፈር አያስተክዝም? ቀን የሰጠው ጨካኝ ተሽቀደድሞ “የመሰዊያውን ቀንድ ስለ ያዘ” በንጹሐን ላይ ሲያላግጥ አንጀት አይታወክም? በወገኔ ሴት ልጅ ድንኳን ግፈኛ እንደ እሳት መዓቱን ሲያፈስስ ልብ በውስጥ አይገላበጥም? ድሪቶ በለበሰ ዘመን የሀገር- ዐደራ -በል የምሁር ገመሬ በአደባባይ ዋሽቶና በሕሊናው ላይ በሆዱ ተኝቶ ሲመላለስ አሽቈልቊዬ ሮጬ አቀበት ቧጥጬ የእንባ ዘር ብበትን ሰሚ አይኖረኝም ወይ?
ያላለቀሰ ዐይን ለምን ተፈጠረ? እንጀራ ይጠግቡ ዘንድ “ነፍስ ያላወቁ” አፍላዎቻችንን በገፍ እያስጫኑ የሚነግዱ አረመኔዎች በዐመፃ ደመወዛቸው ሲሰቡ ያልዘገነነው ነፍስ ምኑን አለ ይባላል? ከሚያቃጥል የረኃብ ትኵሳት የተነሣ ቍርበታችን አልከሰለም? ዐጥንታችን አልገጠጠም? የነድንቡሼዎች ፊት ከሥቶ አልሞገገም?
ስንት ሕይወት ሲመክን፣ ባለ ሥልጣን ሲጨክን እሮሮ ማሰማት የሚጠበቅ ነው። ምድር በዳዴ ስትሄድ ማጕረምረም ብቻ ምን ይረባል? ይለቀሳል እንጅ። ከድኻው ሌማት የቈረሱ “ጅቦች”፣ ይኸ አልበቃ ብሏቸው፣ በደሙ ሲያጠቅሱስ አይለቀስም ወይ? በእንባው ሲያጥኑ አይጐረብጥም ወይ? በላቡ ሲዋኙ አያሠቅቅም ወይ? አይጥና ጥንቸል በሳሎናቸው ለማሳደግ ሚሊዎን ዶላሮችን የሚመዠርጡ ኀያላን ባለጠጎች በሞሉበት ዓለም፣ አውሬነት በሰው ገላ የተገለጠበት አይሲስ (ISIS) ይሉት የጭራቅ መንጋ ያሳደዳቸው፣ “በአገርህ አስጠጋኝ፣ መሸ አዳሪ ነኝ” ባይ ስደተኞች ባሕር ሲውጣቸው መስማት አያሳምም ወይ? እሳት ከሚነድበት ምድር ወደ ተሻለው የዓለም ክፍል ነፍሱን ለማሰንበት ከቤተ ሰቦቹ ጋር የተሰደደው ሕፃኑ አይላን ኩርዲ በቱርክ (ቦድረም) የባሕር ዳርቻ ክንብል ብሎ … በለጋ ፊቱ ድፍት እንዳለ ማየት አቅል አያስትም ወይ?
መጽሐፍም ይህን ይመሰክራል። ኤርምያስ ነቢዩ፣ “ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዐይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ” (ሰቈ. 2፥11) እያለ አላማጠም?። አለቆች ጊዜ ላመጣው ፈሊጥ እያሸበሸቡ ለበኣል ሲያረግዱ ቅስም ይሰብራል። መራር ዘመን ሲመጣ ማልቀስ ምርጫ እንጂ አማራጭ አይደለም፤ ወደ ሰማይ ይጮኹታል።
መሉ ጽሑፉን ለማንበብ “አዳም እና ሔዋን” መጽሔት ቁጥር 3 ያንቡ
www.Adamenahewan.com

One comment

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *