የክርስትያን መጽሐፍት ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ

የክርስትያን መጽሐፍት ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ

በፍሬ ነገርና በሥነ መለኮታዊ ሚዛናዊነት ግልጽ በኾነ መንገድ የተዘጋጁ መጽሐፍት አሉን  – http://shop.tsega.com/books

www.Tsega.com is the place for Christian Media Resources from Ethiopia. Our passion at Tsega Christian Media is to further the Kingdom of God with media resources. Within the last few years the meaning of “Christian Media” has changed dramatically. The possibilities have gone from being broadcast and impersonal, to social, reactive and interactive, with an explosion of opportunity to impact and share with the world of believers and non-believers directly and personally. This fact is both exciting and daunting.

We are here with Media materials to impact the world of believers and non-believers. Visit our books at http://shop.tsega.com/books

Tsega@Tsega.com

ስለአንድ በኢትዮጵያ የተጻፈ መጽሐፍ የተሰጡ አስተያየቶች

በርግጥም በቅሎዋ፣ እንደ ልማዷ፣ ደንብራለች። በተቀመጡባት፣ በራሷ፣ በቅርቧ ባሉት እና በንብረት ላይ አደጋ እያደረሰች ነው። ጌታዋም፣ እርሱም ደግሞ እንደ ልማዱ፣ የሚገሯትን ሰዎች (እንደነ ሰሎሞን እና እንደነ ማነው ስሙ? ያሉትን)፣ የተለያዩ የበቅሎ መግሪያ መሣሪያዎቹን በማስያዝ ከየአቅጣጫው እያስነሣላት ነው።

እናንተዬ! እኔስ በእግሯ ሰካላ፣ በአፏ ዛብ፣ የሚኾንበትን ቀን ናፈቅሁትም፣ ፈራሁትም። መናፈቄ እርሷም፣ እንደ ልማዷ፣ እንደገና ወደ መንገዱ ተመልሳ፣ እንደገናም በወግ ዕቃዎቿ ሁሉ አጊጣ፣ የምትሰግርበት ቀን (የተሐድሶ ቀን) ስለሚኾን ነው። መፍራቴ ግን “የልጆቿን ምክር አልሰማ ብላ መከራ ሊመክራት ይሆን?” ብዬ ነው።

በቀለ ወልደ ኪዳን (መጋቢ) 
ቀጠና ሁለት ሙሉ ወንጌል አማኞች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን 


 እነሆ አንድ ጩኸት! 

ጽሐፉ ባነሣው ርእሰ ነገር የተነሡ ጥያቄዎች በሚገባ ተመልሰዋል፤ የሥልታዊ ነገረ መለኮት ገጽታ አለውና በየሥፍራው ተመሳሳይ ታሪካዊ እውነቶችን ዋቢ እያደረገ ዳግም እንዲደመጡ በማስተጋባት፣ “ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፣ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት” (ዕብ. 2፥3)የሚል መንፈስ የሚታይበት ዕጹብ የዕቅበተ እምነት ሥራ ነው! በሥነ ጽሑፍ ደረጃው የልቀት መሥመርን ያሠመረ ከመኾኑም ባሻገር ምሁራዊ ቃናው ተጨማሪ ተአማኒነት ሰጥቶታል፤ ለዚህ ነው ይህንን መጽሐፍ ነጋሪ ብቻ ሳይኾን አስተማሪ ኾኖ ያገኘሁት። መማር አልጨረስሁም ለሚሉ ሁሉ፣ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ፣ በርእሰ ጕዳዩ ሊማሩበት ይችላሉ። ይህ መጽሐፍ የዘመን ጩኸቶችንና ያልተሰሙ ድምፆችን ያሰባሰበና ከዱር ጕዞ መላሽ ነው፤ የላይኛው ሳይነግረን ፈረደብን እንዳይባል በሰው በኩል ለሰው በልካችንና በቋንቋችን የተነገረ እነሆ አንድ ጩኸት! ቤተ ክርስቲያን ትሰማው ይኾን?

ሰሎሞን ጥላሁን 
ሬጀንት ዩኒቨርሲቲ፣ ሀገረ አሜሪካ “የደነበረው በቅሎ”


 

 “ተሳስቼ ነበር” 

በቅርቡ ባላሳትመውም፣ ውሎ አድሮ ለንባብ የማበቃው፣ መጽሐፍ አለኝ። መጠሪያው ተሳስቼ ነበር የሚል ነው። የዚህን ዝግጅት አንጓ መልእክት ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በማቴቴስ መጽሔት ላይ ቤተ ክርስቲያንን መትከል ወይስ መክፈት በሚል ርእሰ ነገር ላይ “ተሳስቼ ነበር” ብዬ መጻፌን አልዘነጋውም። ይህንንም ያደረግሁት በአደባባይ ለተገለጠ ስሕተት የአደባባይ ምልሽ በመስጠት ማረም ግድ መኾኑን በማመን ነበር።

ዘንድሮ ደግሞ ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን የደነበረው በቅሎ በሚል [ርእስ] የአስተምህሮ ልጓም አስፈላጊ መኾኑን ሊያሳውቀን ተነሥቷል። መጽሐፉ ምጥን ገጾች ያሉት ቢኾንም፣ የእርጋታ ንባብን ይሻል። ግራ ቀኙን በማጤን፣ ለካስ እንደ ቤርያ ሰዎች ካልኾንን፣ ወየውልን ያሰኛል። መጽሐፉ ራሳችንን አካትተን ሁሉን እንድንፈትሽ ግድ ይለናል። ፍተሻው ተሳስቻለሁ፣ ተሳስተናል ወይም አስተውናል በማሰኘት ከከንቱ ሩጫችን ይገታናል።

በርግጠኛነት ዛሬ ብዙ ምእመን፣ ብዙ ሰባኪ፣ ብዙ መጋቢ፣ ብዙ ዘማሪ በሀገሪቱ እየተርመሰመሰ ነው። አብዛኛው በዕለታዊ ኑሮ “ጠበል ፈለቀ”በተባለበት ስፍራ ፈጥኖ በመድረስ ያገኘውን እየሸመተ ነው። ይሕ ዐይነት ሸመታ ደግሞ ጕዳትን ያስከትላል። የደነበረው በቅሎ ይህን ሊያሳየን ተጻፈ። እንኪያስ የክርስቶስ ነኝ ያለ ሁሉ ዘመኑ ሳያልፍ ከወዲሁ እንዲጠነቀቅ ጥሪ ቀርቦለታል።

ሰሎሞን፣ በመጋቢነት ጸጋውና ጥሪው በ የትሩፋን ናፍቆት መጽሐፉ የመከረንን ምክር አሳድጎ፣ ዛሬም ሁሉን በመመርመር ፍሬያማ ኑሮን በቃሉ መሠረት እንመዝንም እንኖርበትም ዘንድ ሁላችንን ይጋብዛል።

ስሜ ታደሰ (መጋቢ) 
የኢትዮጵያ ባይብል ባፕቲስት ቸርች ፌሎሺፕ ፕሬዚዳንት 


ሰማዩን ጥቋቍር ደመናዎች አንዣበዉበታል። ደመና ገፋፊ ብሩህ ጸሓይ የቃሉ ወገግታ ነው፤ ደመና በታኝ ብርቱ ነፋስ ቅዱስ መንፈስ ነው። ወንድማችን ሰሎሞን ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበትን እውነታ፣ በብልኃተኛ ጥጥ ፈልቃቂ አያያዝ እየጐለጐለ አውጥቶ፣ አሳየን፤ አልባሌውን ከኹነኛው እንድንለይ አነቃን። ታዲያ እኛ ምን እናድርግ? ጕልጕሉን ጥጥ እያባዘትን፣ እየነደፍን እያደራን ጥሩ ሸማ እንሥራ፤ ሙሽራይቱንም እናልብሳት።

ንጉሤ ቡልቻ 
ኮምፓስ-ኢትዮጵያ፣ “ቃሉ ያበራል” ፕሮጀክት 


 

አሁን በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና በክርስቲያንነት በምንታወቅ ቍጥራችን ጥቂት ባልኾንን ሰዎች ዘንድ የሚታየውን ሕይወት ሳስብ፣ “እኔ ነውሬን ወዴት ልሸከም?” (2ሳሙ. 13፥13) የሚለው የትዕማር ጥያቄ ወደ አዕምሮዬ ይመጣል።

በዕድሜ ታናሽ፣ በአዕምሮ ብስለትና በአመለካከት ግን ትልቅና ገና ብዙ ሊያደርግ የሚችለው ወንድማችን ሰሎሞን አበበ በዛጋጀው “የደነበረው በቅሎ” በሚለው መጽሐፍ አማካይነት በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች መካከል የሚታዩትን፣ ሊወገዱ የሚገባቸውንና “የጨውነትና ብርሃንነት” አገልግሎት እንዳንሰጥ ወደ ኋላ የሚጎትቱንን ነገሮች በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ ምን ርምጃዎችን ብንወሰድና ምን ውሳኔዎች ብናደርግ ነውራችን ተወግዶ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋትና ለምድራችን በረከት ለመኾን እንደምንችል በጥሩ ኹኔታ አቅርቦልናል።

ይህንን በፍሬ ነገርና በሥነ መለኮታዊ ሚዛናዊነት ግልጽ በኾነ መንገድ የተዘጋጀ መጽሐፍ አንብቤ ተባርኬአለሁ፤ ማድረግ ያለብኝንም ተረድቼአለሁ። ከዚህም የተነሣ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ቤተሰብ፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶችና የቤተ ክርስቲያን አጋዠ የኾኑ ድርጅቶች መጽሐፉን እንዲጠቀሙበት እመክራለሁ፤ አበረታታለሁም።

ሺፈራው ወልደ ሚካኤል
ከልጆች ዕድገት ሥልጠናና ምርምር ማእከል (CDTRC) “የደነበረው በቅሎ” 


“እነሆ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው እናገባለን፣ ሥጋቸውንም እንመራለን” (ያዕ. 2፥3)፡፡ ሐዋርያው ይህን ያለው በአስተማሪነት ዐውድ ውስጥ መኾኑን ልብ ይሏል(ቍ. 1-2)፡፡ የአፍ ንግግራችን፣ አስተምህሯችንና ጠባያችን በርግጥ “ልጓም”— የቅዱስ ቃሉና የመንፈስ ቅዱስ ቍጥጥር — ያሻዋል፡፡ ቍጥጥርን ግን ማን ይወዳል? “የጌታ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” በማለትና ቃሉን ያለ መንገዱ በመውሰድ ያለ ቍጥጥር መለቀቅን የምንመርጥ የለንም? መንፈሱ ራስን የመግዛት ቢኾንም (2 ጢሞ. 1፥7)፡፡

በአሽከርካሪው ቸልታም ኾነ በሌላ ምክንያት፣ ከቍጥጥር ውጭ የኾነ ተሽከርካሪ የሚያደርሰውን የንብረትና አሠቃቂ የሕይወት ጥፋት ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ለራሱ የደኅንነት ቀበቶ ያሠረ “ሾፌር” ግን በአመዛኙ ከሚደርስበት የአደጋው ጉዳት ሊያመልጥ ወይም ጉዳቱን ሊቀንስ እንደሚችልም ይነገራል፡፡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳያደርግና “ሳይታሠር” የሚያሽከረክር ሾፌር ግን ከተያዘ ሊቀጣ ይችላል፡፡ አልያም ምክርና ማስጠንቀቂያ መቀበሉ አይቀርም ብለን እናስባለን፡፡ ዓላማው ጉዳትን በመከላከል የተሳፋሪዎችን ደኅንነት መጠበቅ ነው፡፡

ወንድማችን ሰሎሞን፣ በዚህ መጽሐፉ፣ ለራሳችንና ለምናገለግለው ሕዝብ ደኅንነት ስንል ለመቈጣጠሪያው መንፈሳዊ “ልጓም” ሕይወታችንን እንድንሰጥና ይህንንም ሳናደርግ ቀርተን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሰን እንዳንገኝ በወንድማዊ ፍቅር ይመክረናል፤ ያስጠነቅቀናል፤ በ“ነቢያዊ” ጩኸቱም ያነቃናል(የምንነቃ ካለን)፡፡ በእውነት ላይ ቆሞ ማስጠንቀቂያ መስጠትም የእውነተኛ ነቢይ ሚና ነው፡፡ የማስጠንቀቅም ዓላማው የሚመለከታቸውን ሁሉ ከአደጋ ማትረፍ ነውና፣ ይህን አዎንታዊ ውጤት እንጠብቃለን፡፡

እንግዲህ፣ መንፈሳዊ መሪዎችና የቃሉ አገልጋዮች እንደ ኾንን የምናስብ ሁላችን፣ ለራሳችን ስተን ብዙዎችን ከማሳት እንድንተርፍ፣ ከጥፋትም እንድንጠበቅ፣ በሰከነ ልብ ይህን መጽሐፍ እናንብብና እንመከር፡፡ “ከባሰውም ፍርድ” እንድንድንና “መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባርያ…” ለመባል፣ በሞቱ የዋጀንና ለአገልግሎቱ የጠራን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋው ይርዳን(ያዕ. 2፥1፡፡ ማቴ 25፥21)፡፡

ተስፋዬ ጋቢሶ (መጋቢ) 
ከሐዋሣ ሙሉ ወንጌል አማኞች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን


 

“የደነበረው በቅሎ”፦ የአስተምህሮ “ልጓም” ይሻል፡- የተሰኘውን [መጽሐፍ ረቂቅ] አንብቤ ስጨርስ የተሰማኝ ስሜት ደስታና ሥጋት የተቀላቀለበት ነበር፡፡ ደስ ያለኝ እጅግ የተዋጣለትና የጊዜው መጽሐፍ ሊታተም መዘጋጀቱን ዐስቤ ሲኾን፣ ሥጋቴ ደግሞ፣ ከሀገራችን የማንበብ ባህል አንጻር፣ በስንቱ ሰው እጅ ገብቶ ይነበብ ይኾን? ከሚል የመጣ ነበር፡፡ ስለኾነም ሥጋቴ ተወግዶ ደስታዬ ፍጹም እንዲኾን፣ ይህን ጠቃሚ መጽሐፍ አማኞች ሁሉ አንብበው ራሳቸውንና ቤተክርስቲያንን ከዘመኑ የትምህርት ነፋስ እንዲጠብቁ እመክራለሁ፡፡

ጌታሁን ታደሰ (መጋቢ)
የኢትዮጵያ አማኑኤል ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት


መስቀል አልባ ክርስትና፣ ክርሰቶስን ጥግ ላይ ያቆመች ቤተክርስቲያን፣ ሰው ሰው ብቻ የሚሸትት አስተምህሮ የነገሠበት ዘመን እኛ እንደምንኖርበት እንደዚህ ያለ ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡

እኛም ጥቍሩን ጥቍር፣ ነጩንም ነጭ ማለት አቅቶን በምንንገላታበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ይህች መጽሐፍ፣ የክርስትና እምነት በሕይወት መኖሩም ኾነ የዕድሜ ቍጥሩ የሚለካው በአስተምህሮው ንጽሕናና በመጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ ነው ስትል ትሞግተናለች፡፡ ለወጣቱ ትውልድ፣ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀሙ ከባድ ቢኾንም እንኳ፣ ላለንበት ዘመን ወሳኝ መልእክት ይዛለችና፣ ከማንበብ ውጭ ሌላ ምርጫ የለንም፡፡ በተለይም፣ የዩኒቨረሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች እንዲሁም ምሩቃን እንዲያነብቧት አበረታታለሁ፡፡

ዘላለም አበበ 
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት (EvaSUE)ፕሬዚዳንት


በኢትዮጵያ ያለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከምንጊዜውም በበለጠ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ትገኛለች። ቀድም ባለው ጊዜ ስሕተት ሲባሉ የነበሩ ትምህርቶች ዛሬ በየአትሮኖሱ ላይ፣ በታላቅ ድፍረት፣ “ዐዲስ መገለጥ” ተብለው ይለፈፋሉ። ይህ ሳያንስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸው ልምምዶች አብያተ ክርስቲያናትን መሙላታቸው ፀሓይ የሞቀው ጕዳይ ነው። በተጨማሪም፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መዛነፍ የብዙ አማኞችን ሥነ ምግባራዊ ዐቋም ፈትኗል፤ ብዙዎችንም በማዛል ከሩጫው ሜዳ አስወጥቷል። ሰሎሞንም፣ በሰላ ብዕሩ፣ ይህንን ክርስትና መሳይ ነገር፣ እንደ ይሁዳ፣ “ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት” (ይሁዳ 1፥3ዐመት) ስንል “እንድንጋደለው” ይሞግተናል፤ ይሸነቁጠናል።

 

የደነበረው በቅሎ ክፉ ዜና ለፋፊ ጽሑፍ አይደለም። ይልቁንም ለዚህ “ድንበራ” የመንስኢ ምክንያቶችን በመግለጽ በዚሁ ከተቀጠለ ቤተ ክርስቲያን እያጋጠማት ያለውን አደጋ የሚያትት ቢኾንም፣ ገና ተስፋ እንዳለ በማብሠርም ከቈዘምንበት እንድንነሣ የሚያበረታታ ነው እንጅ።

ድግግሞሹ ከመብዛቱ የተነሣ ሐሰትን ከእውነት ለመለየት ጆሮዎቻችን በደነዘዙበት በዚህ ዘመን ይህ መጽሐፍ ትንቢታዊ በኾነ መልኩ ከዕንቅልፋችን የሚያነቃ ደወል ይመስላል። አማኞች የዚህን መጽሐፍ ጥሪ ሰምተው ወደ መጽሐፉ ከተመለሱ፥ በኢትዮጵያ ያለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ይበልጡኑ ታብባለች፤ እግዚአብሔርም በምድራችን ላይ ይከብራል።

ስለዚህ ሰሎሞንንና እርሱን የሚመሳስሉ ለቤተ ክርስቲያን መታደስ የሚተጉና በጤናማ ነገረ መለኮታዊ አስተሳሰብ የዳበሩ አገልጋዮችን እግዚአብሔር እንዲያበዛልን እየለመንን ይህን መጽሐፍ በጥሞና በማንበብ ተግባራዊ ምላሽን እንስጥ። ሰሎሞን የሩጫው አካል የኾነችንውን ይህችን መጽሐፍ እንካችሁ ብሎናል፤ እኛም ሰሚ ጆሮዎቻችንን አንንፈገው።

ዮሐንስ ሞሐመድ (መጋቢ) ከቦስተን፣ ሀገረ አሜሪካ

 


                                     Abiyot Gurasho Friday, 28 November 2014 16:47

መጽሐፉን ባላነበውም ከርዕሱ እንደምረዳው ልጓም የሚሻው የጊዜያችንን መጣፍያውን ያጣ የሚመስል የቤተክርስትያን ገጽታ የሚያስቃኝን ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ለተፈጠረው የአስተምህሮ መፋለስ የአባቶች ድርሻ በተለይም በመጽሃፉ ላይ አስተያየት የሰጡትን ጨምሮ ድርሻ አለበት ብዬ ልሞግት ደፍራለሁ›› ምክንያቱም አባት የሌላቸው ልጆች ይወለዱ ዘንድ፤ በትውልዱ መሀል ክፍተት ይፈጠር ዘንድ አስተዋጽኦ ነበረቸው የሚል አመለካከት ስላልኝ ነው፡፡ የአባትነት መንፈስ ስፍራውን ሲለቅ አባት የሌላቸው ወይም አባቶቻቸውን የማያውቁ ..የባህሩን መከፈል ታሪክ ያላነበቡ..ወይም ያልተነገራቸው በምድረበዳ የተወለዱ…መና ብቻ በልተው ያደጉ….ጦርነት የማያውቁ..ቅምጥል ልጆች.. እዛም እዚህ ይፈለፈሉ ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ ስለዚህ የአባቶች ቸልተኝነት አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላልና ከአስሩ ጣቶች የሚበዙቱ ወደእናንተ የተሰነዘረ እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ እግዚአበሔር ይርዳን፡፡ (ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።ገላ 1፡8) –

One comment

  1. ፓ/ር ተፈራ አብርሃም says:

    በኢትዮጵያ የሚታተሙ ጠቃሚ የአማርኛ መጻሕፍትን በድረገጻችሁ ላይ በቀላሉ ማዘዝና መግዛት መቻሌ አስደስቶኛል:: የዋጋችሁ ተመጣጣኝነት ሌላው ሲሆን በሁለት ቀን ስለደረሰኝ አመሰግናለሁ:: ዲያስፖራው ሊያነባቸው የሚገባው ብዙ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጻፉ መጻሕፍት አሉ:: ጌታ ያበርታችሁ!
    ተፈራ ነኝ ከካልጋሪ ካናዳ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *