Tsega.com – “ስለ ወንጌል” – ከዘማሪ ደረጀ ሙላቱ

Tsega.com – “ስለ ወንጌል” – ከዘማሪ ደረጀ ሙላቱ

www.Tsega.com: በደመቀው የአምልኮ ዝማሬ መካከል ፊቱ የተጠባበሰና አንድ እጁ በአደጋ የተቆረጠ ሰው በተቆረጠው እጁ የደህናውን እጁን መዳፍ እየመታ ይዘምራል፡፡ ዘለግ ያለ ቁመና ያለው ቀጠን ያለ በግምት ሰላሳ ሶስት ዓመት አካባቢ የሚገመት ወጣት ነው፤ ከአጠገቡ የሚያማምሩ ሁለት ሕጻናት ቆመው ወደ ቀኝና ወደ ግራ እያዩ አንዴ ይዘምራሉ አንዴ ወሬ ያወራሉ፡፡

መዘመሬን ትቼ ሰውየውን እያየሁ በአንድ ዘመን በነበረ ጦርነት ወይም በአደጋ አካሉን ያጣ ሰው እንደሆነ አስቤ መለስ አልኩና “ለምን በግድ አጨብጭቡ ይሉናል” ብዬ ስማረር የነበርኩት ሰው በሰውየው ምስጋና ተኮንኜ ሳላስበው ከመጠን በላይ አጨበጨብኩ፡፡

በዚያን ቀን ሰባኪው ‹‹የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች›› በሚል ርዕስ ነበርና የሚሰብከው ጉባኤው በታላቅ ዕልልታና በደመቀ አሜንታ መልእክቱን ያደምጥ ነበር፡፡

ያለወትሮዬ ያንን እጁን በአደጋ ያጣውን ሰው መላልሼ መመልከቴን አላቋረጥኩም፤ በመሀል አንዲቷ ሴት ልጁ ወደ ጆሮው ጠጋ እያለች ስታዋራው በፍቅር በተሞላ ፊት ይመልስላት ነበር፤ ወዲያው ከአይኖቿ እምባ ሲወርድ ተመለከትኩና ካለሁበት ተነስቼ ወደ ውጭ ይዣት ወጣሁ፡፡

በላይዋ ላይ የቆየው ልብሷ፤ በእንቅፋት የቆሳሰለው እግሯን ተመልክቼ ቁጢጥ ባልኩበት በሀሳብ ተመልሼ ለምን እንደምታለቅስ ጠየኳት፤

የተዋቡትን አይኖቿን እያቁለጨለጨች ‹‹እርቦኝ ነው›› አለች በተኮላተፈ አንደበቷ፤

ከቤተ ክርስቲያናችን ፊት ለፊት ካለው ሱቅ የምትበላውን ብስኩትና ሚሪንዳ ገዝቼላት ውስጤን የሚታገለውን የሰው ልጅ ችግር ጉዳይ ብሶት ዋጥ አድርጌ ረሃቧን ስታስታግስ እያየሁ ቆየሁ፡፡ ረሀቧ ረገብ እንዳለላት አይቼ፤ ‹‹ሚሚዬ ስምሽ ማን ነው?›› አልኳት

‹‹ሽለወንጌል›› አለችኝ በፈገግታ ‹‹ስለ ወንጌል?›› አልኳት ለማጣራት ብዬ፤ ጭንቅላቷን ነቅንቃ ‹‹አዎ›› አለችኝ   በስሟ ዙሪያ አንድ ታሪክ ይኖር ይሆን እያልኩ በልቤ ማውጠንጠን ጀመርኩ፤ አሁን ፕሮግራሙ ወደ ማለቂያው እየደረሰ ስለነበር የስለ ወንጌልን አባትና እህቷን ለማግኘትና ምሳ ለመጋበዝ ወሰንኩ፡፡ ይህንን እያውጠነጠንኩ ሳለሁ ስለ ወንጌል ከአጠገቤ በራ ስትሮጥ ከሀሳብ ተመልሼ በአይኖቼ ተከተልኳት፡፡ ከልኩ በላይ ኮት ወደ ለበሰው አባቷ ነበር የሮጠችው፡፡

ኑሮ እንደተፈታተነው ፊቱ ይናገራል፤ ቢሆንም ግን የውስጡ ደስታ በፊቱ ላይ ከመከራው በላይ ይታያል፡፡ ጎንበስ ብሎ ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ ተሳስመን ስንጨርስ       ‹‹ይሁን እባላለሁ›› አለኝ፡፡

ወዲያው አእምሮዬ ‹‹ስለ ወንጌል ይሁን›› ብሎ የልጁን ስም አገናኝቶ የበለጠ ስለዚህ ስም አመጣጥ ለማወቅ ያለኝን ጉጉት አፋጠነብኝ፡፡     ‹‹ምሳ አብረን ብንበላስ ወንድሜ ይሁን?›› አልኩት እጁን እንደጨበጥኩ   ‹‹መልካም! እግዚአብሔር ይባርክህ!›› አለኝ

ወዲያው አንደኛዋንም ልጁን ከሰዎች መሀል ፈልጎ ይዟት መጣ፡፡ አብሮት የመጣውን የቤተ ክርስቲያናችንን ወንጌላዊ ወንድም ይሁንን ምሳ ልጋብዘው እንደፈልኩ ነገርኩትና ስንጨርስ እርሱ ቤት ማረፉን ነግሮኝ እዚያ ልመልሰው ተነጋግረን ተለያየን፤

‹‹ይህችኛዋ ብርሃን ትባላለች ስለ ወንጌልን ስድስት ዓመት ትበልጣለች፤ ጌታን ያገኘሁት እርሷ ከተወለደች ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፤ ለዚያ ነው ብርሃን ያልኳት›› አለኝና እራስዋን እያሻሸ በፍቅር ፊት ይመለከታት ጀመር፡፡ ውስጤ በአንድ በማላውቀው ስሜት እየተናወጠ ወደ መኪናዬ ይዣቸው ሄድኩና አስገባኋቸው፡፡

‹‹ምን አይነት ምሳ ነው መብላት የምትፈልጉት ወንድም ይሁን?›› አልኩኝ ፍላጎታቸውን ለማወቅ፡፡     ‹‹ጌታ ያዘጋጀውን እንበላለን›› አለ በፈገግታ

ብዙ ምርጫ ወዳለበት ሆቴል መኪናዬን እያሽከረከርኩ ጥያቄዎቼን መወርወር ጀመርኩ፡፡

‹‹ባለቤትህ ከእናንተ ጋር አልመጣችም?›› ብዬ ወዲያው፤ ወይኔ በሕይወት ባትኖር እነዚህ ልጆች ላይ የሐዘን ድባብ ልጥል ነው አልኩኝ በልቤ ጥያቄው ከአፌ ከወጣ በኋላ፡፡

‹‹አይ እርሷ አልመጣችም እቤት ናት›› አለኝ፤ እኔም ተነፈስኩ፡፡

ምሳችንን እየበላን ከአዲስ አበባ ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር በሚርቅ አካባቢ እንደሚኖሩ ነገረኝ፡፡ ወንድም ይሁን ታሪክ አጣፍጦ መናገር ይችላል፡፡ በንግግሩ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ጣል ማድረግ ግድ የሆነ እስኪመስል ንግግሩ ሁሉ በቃል የተሞላ ነው፡፡ ቃሉን እየጠቀሰ ታሪኩን ሲናገር የራሴን አካሄድና ንግግር ለመኮነን ቃጣኝ፡፡

‹‹አሁን የምኖርበት አካባቢ የተወለድኩበት አካባቢ አይደለም፤ ያልተነገረላቸው ይሰማሉ እንደተባለው ቃል በወንጌል ምክንያት ተሰድጄ ነው የመጣሁት፤ ከአንዱ አገር ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላው ሂዱ አይደል የሚለው እንደዚያ ሆኖ ነው አሁን ወዳለንበት የመጣነው የዛሬ ስድስት አመት›› አለኝ በሀሳብ ጥቂት ዓመታት ተጉዞ እያሰላሰለ፡፡

ቤተሰቦቼ ለወንጌል ዝግ የሆኑና አክራሪዎች በመሆናቸው እኔና ባለቤቴ የወይን እሸት ጌታን ስንቀበል ስደት በረታብንና መሬታችንን ሸጠን ተሰደድን፤ ጌታ ያመላከተን ቦታ አሁን ያለንበት በመሆኑ በዚያ ካሉ ጥቂት ወገኖች ጋር ጌታን በማምለክ መኖር ጀመርን››

ንግግሩን አቋርጨ ‹‹ስለ ወንጌል የተወለደችው እዚህ ነው?›› አልኩት

ለጥቂት ሰከንዶች በትካዜ መሬት መሬቱን አይቶ እምባ ያቀረሩ አይኖቹን ለመግታት እንደገና ወደ ጣራው ቀና አለ፡፡ ያኔ አንዳች ስሜት ነዘረኝ፡፡ እንባውን በመዳፉ ጠረግ አደረገና፤

‹‹የዛሬ ሶስት ዓምት ባለቤቴ ስለ ወንጌልን ለመውለድ አንድ ወር ሲቀራት በነበርንበት አካባቢ ሀይለኛ ስደት ተነስቶ ነበር፤ እኔም የጌታ ጥሪ ወደ እኔ በመምጣቱ በአካባቢው ባሉ ገጠር መንደሮች ጭምር ወንጌል እሰብክ ስለ ነበር የአሳዳጆች ዋና ኢላማ እኔና ቤተሰቤ ነበርን፡፡

እግዚአብሔር መልካም አምላክ ነው! ቅዳሜ እለት ባለቤቴ በጠዋት ወደ አንዲት እህት ቤት ብርሃንን ይዛ ሄዳ ነበር፤ ልክ ሦስት ሰአት ላይ የስደቱ ግለት ቅዱሳንን በመግደል ጭምር የታቀደ ስለ ነበረ የአንዳንዶች ቤት መቃጠል ጀመረ፡፡

በዚህ ሰአት እኔ ለጸሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመጣሁበት እዚያው ነበርኩና በርካታ መጥረቢያና ገጀራ የያዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ግቢ ገቡና ያገኙትን ሰው መምታት ጀመሩ፡፡ ወደ እኔ ሲመጡ

‹‹ይሄ ነው ዋናው በለው! ግደለው›› እያሉ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ያለውን ነገር ማስታወስ አልችልም ምክንያቱም ራሴን ያገኘሁት በጭላንጭል ማየት በምችልበት ሁኔታ ፊቴ በፋሻ ተጠቅልሎ በሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡››

በትዝታ ሦስት አመታትን ወደ ኋላ እያሰበ ሽምጥ የጋለበው የወንጌል ሰባኪ ከሞት ጋር ያደረገውን ትግል እንደሚያውጠነጥን አሰብኩ፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ በውስጤ እያደነኩ በውል የማላውቀውን ያንን በቅዱሳን ደም የጨቀየ መንደር በምናቤ መሳል ጀመርኩ፡፡

አዳኝ አጥተው የሚራወጡ የቅዱሳን ልጆች በፊቴ ድቅን አሉብኝ፤ ሳላስበው እንባዬ በጉንጮቼ መውረድ ጀምረ፤ ይሁን ከትዝታ ባህር ብቅ ብሎ ትረካውን ሲጀምር እኔም ከሄድኩበት ተመለስኩ፡፡

‹‹ከሁለት ወራት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ክፉኛ የተጎዳው ፊቴና ጭንቅላቴ እንደምታየው ጠባሳው ቢኖርም ስለ ዳነ ከሆስፒታል ወደ ቤቴ ተመለስኩ፤ የቀኝ እጄም በላዬ ላይ አልነበረም፤›› አሁንም እምባ የተናነቀው ግን የድል አድራጊ ሰው ስሜት፤ ‹‹ወደ ቤት ስገባ ቅዱሳን በማልረሳው ሁኔታ አቀባበል አደረጉልኝ፤ የልቤን ጽናት ይበልጥ ያበረታ ዝማሬ ይዘምሩ ነበር››

‹‹ልብህ ጽኑ ይሁን አትላላ ጠንክር

ባመንክበት ጌታ በፍጹም አትፈር……››

ስሜቴ ድብልቅልቅ ያለ ነበር፤ ልጆቼን ሳይ፣ አንዳንድ ወገኖችን ሳይ፣ ፊታቸው እንደ እኔ በስደቱ ምክንያት የተጠባበሰ የወንጌል ተጋዳዮችን ፈገግተኛ ፊት ስመለከት የጀግንነትና የወንጌል ባላ አደራዎች መንገድ እየታሰበኝ ደስታም ሃዘንም ለቅሶም በላዬ ላይ ተፈራረቀ፡፡››

በሆስፒታል ባገኛቸውም ሙሉ ለሙሉ ድኜ ወደ ቤት ስመለስ ልጆቼንና ሚስቴን ሳይ አንድ ድምጽ ልቤን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረ ‹‹ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ›› ይህንን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፤ ከዚያም በተቀመጥኩበት አይኖቿ እንደ ባውዛ ቦግ ቦግ ያሉ የምታምር ቀይ ሴት ሕጻን ጉልበቴ ላይ አሰቀመጡልኝ፡፡

ያን ጊዜ ነው ስሟን ያወጣሁት፤ የሆነብንን ሁሉ አሰብኩና የሆነብን ሁሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ስለሆነ ስሟን ስለ ወንጌል የሚሆንብን ሁሉ ይሁን በማለት ‹‹ስለ ወንጌል ይሁን›› ብዬ ጠራኋት፡፡››

ወንጌል ሙሉው መነበብ ካልቻለ በፈተና መሀል መቆም አይቻልም፡፡ በዚያ መንደርም ሆነ ቀድሞ በነበርኩበት በቤተሰቦቼ አገር ጌታን ባገኘን ወቅት የደቀ መዝሙር ትምህርት ስንማር ከክርስቶስ ኢየሱስ እጅ ስለምንቀበለው በጎና መልካም ነገሮች ብቻ ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ልንቀበለው ስለሚገባ መከራም ጭምር ይነግሩን ነበር፡፡

ዛሬ ባካባቢያችን በእነኚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ብዙዎች ወደ ጌታ መጥተዋል፤ ከአሳዳጆች አብዛኞቹ ኢየሱስን አግኝተዋል፡፡ ወንጌልን በደስታ እንሰብካለን፤ ሰይጣን በምንም ሊያስፈራራን አይችልም፣ ሊቋቋመን አይችልም እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋና አቅም ነፍሳችንን ሳይቀር ለመገበር ከትላንት ይልቅ ዛሬ የቆረጥን ሆነናል››

ይሁን ልቡ የአንበሳ ልብ ነው፤ ኑሮውን ጠየኩት፤

‹‹ኑሮስ እንዴት ነው ወንድሜ ይሁን?››

‹‹አሁን የምኖረው ኑሮ በክርስቶስ ላይ ባለኝ ዕምነት ነው አላለም ሐዋርያው! እየኖርን ነው፤ እግዚአብሔር ይመስገን!››

‹‹ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጥህ ደሞዝ ልጆች ይዘህ ለመኖር ይበቃሀል››

‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚል እኮ ማንኛውም ኑሮ ይበቃዋል ይበቃናል›› መልሱ አጭርና ቁርጥ ያለ ነው፡፡

የራሴን ኑሮ ተመለከትኩ ያለኝ አልበቃና አላረካ ብሎኝ መሰቃየቴ፣ የተሻለ ምድራዊ ቤት ለመስራት ለላይኛው ቤቴ ግዴለሽ መሆኔ፣ ከስራ ስራ እያማረጥኩ ከፍ ያለ ደሞዝ ለማማረጥ ለነፍሴ በቂ ግዜ ሳልሰጥና ሳላርፍ መኳተኔ፣ ስለ ወንጌል ብሎ ያለኝ ይበቃኛል የሚለውን ለመደገፍ ለገጠር ወንጌል ስርጭት እጃችሁን ዘርጉ እየተባለ በየእሁዱ ሲነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ መኖሬ በአንድ አካላቱን ሁሉ ስለ ወንጌል አጥቶ በደስታ ዛሬም በአንድ እጁ እያጨበጨበ በሚያመልክና እኔ ከንፈሬን በመጠጥኩለት ደሃ መሳይ የወንጌል ባለጠጋ የመንፈስ ድህነቴና አቅመ ቢስነቴ ተጋልጠውብኝ እርሱ ባለጠጋ፤ እኔ ደግሞ ከርሴን ለመሙላት የምሯሯጥ ደሃ መሆኔን በመረዳት እግሮቼን አነባብሬ ቡና እየጠጣሁ በምድራዊ ቁሳቁስ ጥርቅም ሀሳብ ተይዤ ያሳለፍኳቸው በርካታ ከንቱ ቀናት ትዝ አሉኝ፡፡

በዚህ መሀል ይሁን ‹‹አሁን አዲስ አበባ የመጣሁት በኛ መንደር ዙሪያ ወንጌል ለመስበክ ሰፊ እቅድ ስላለን ለዚያ የሚረዱ በራሪ ወረቀቶችን ለማግኘት ነው›› አለ፡፡

‹‹ለወንጌል የቆረጠ ትኩስ ልብ›› አልኩኝ በልቤ፡፡

ይሁንን ወንጌላዊው ቤት ካደረስኩ በኋላ አድራሻውን ተቀብዬው ተሰናብቻቸው ወጣሁ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የመኖር ናፍቆቴን የሚረብሽ ማንነት ውስጤ ተፈጠረ፡፡ ልሸሸው የማልችለው አንድ አካል በደሜ ውስጥ ይራወጣል፡፡ እጆቼን ባየሁ ቁጥር ‹‹ስለ ወንጌል ይሁን!›› የሚል ድምጽ አዕምሮዬ እስኪናወጥ ይጮህብኛል፡፡

የምወዳቸውና የምመኛቸው ዘመናዊ የተድላ ጉዳዮች ሁሉ ‹‹ራስ ወዳድ አትሁን!›› እያሉ ጣታቸውን የሚቀስሩ ሰባኪዎች ሆኑብኝ፡፡ ይሁንን መርሳት አልቻልኩም፤ የስለ ወንጌል የእምባ ዘለላዎች እየተወረወሩ አናቴ ላይ ይወድቁብኛል፤ በመኝታዬ ላይ ሆኜ ጣራውን ሳየው ስለ ወንጌል ምን አደረክ? ስለ ወንጌል ምን ጎደለብህ? ስለ ወንጌል ምን ተውክ? የሚሉ ጽሑፎች እየተነበቡ እንቅልፌን እየቀሙ አስቸገሩኝ፡፡

ጌታ ኢየሱስ ስለ እኔ ሁሉን ትቶ መምጣቱን ስዘምር የደስታዬ ብዛት እምባዬ እስኪረግፍ የሆነባቸው ቀናት ብዙ ቢሆኑም አሁን ግን ውለታው ሲዘመር የእኔስ ድርሻ የሚለው ጥያቄ እየዘለልኩ የማመልከውን ሰው ሰከን አድርጎኛል፡፡

“ይህን ያህልማ መተከዝ አይገባም” ብዬ ራሴን ለማረጋጋት ስጥር ‹‹ትካዜን ምን አመጣው? ጉዳዩ ተገቢውን ሰርተሀል ወይ ነው እንጂ›› ይላል ያ ውስጤ የሚሮጠው አካል፡፡

ለአንድ ድርጅት የሰራሁት የኮንትራት ስራ ተጠናቆ ሁለት መቶ ሺህ ብር መውሰድ እንደምችል በስልክ ሲነገረኝ በሌሎች ግዚያት እንዲህ ያሉ ስኬቶችን ለጓደኞቼ ወዲያው መናገርና መገባበዝ የምወደው ሰው ዛሬ ደስታዬ ሩብ ያህልም አልሆነም፡፡ ‹‹ጤነኛ ነኝ?›› ብዬ ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡

ነፍሴን የያዘው ጉዳይ ከኖርኩበትና ከከረምኩበት ልምድ ሊያወጣኝ እየታገለኝ ስለሆነ በዚህ ትግል የተፈጠረ ህመም ላይ መሆኔን ማሰብ ጀመርኩ፡፡

አንድ ለራሱና ለራሱ ብቻ ለመኖር የሚታገል፤ አስራትና መባ በመስጠቱ የተረጋጋ፣ አልፎ አልፎ በየባንኩ ከተከመረ ገንዘቡ ላይ ለአንዳንድ አገልግሎትና ለተቸገሩ ሰዎች ጣል የሚያደርግ ነገር ግን ለሀብታምነት ከሚሮጥበት የሩጫ መስመር ለወንጌል ጠቀም ያለ ነገር ቢሰጥ ከአካሉ ላይ ስጋ የተቦጨቀበት ያክል የሚያመው ሰው መሆኑን እያመነ ያለ ግን ለመሸሽም የሚሞክር ሰው ታየኝ፡፡ ያም ሰው እኔው ነኝ፡፡

የመኪናዬን መስኮቶች ዘጋሁና ‹‹ተድላ አትሽሽ›› ብዬ ስሜን ጠርቼ ጮህኩ፡፡ ሽሽት የትም እንደማያደርስ ማመን ጀመርኩ ከተንጋለልኩበት ተነስቼ ከስልኬ ውስጥ የአንድ ሰው ቁጥር ተጫንኩ ‹‹ይሁን ደስታ››

የተረጋጋ ሰው ድምጽ ‹‹ሀሎ›› ‹‹ሀሎ ወንድም ይሁን ሰላም ነህ?››

‹‹ሰላም ነኝ ጌታ ይመስገን ማን ልበል?››

‹‹ወንድም ይሁን ተድላ ነኝ››

ይሁን ወደ አገሩ አልተመለሰም፡፡ ያሰበውን ያህል በራሪ ወረቀት ለማግኘት አልቻለም፤ ለዚህም ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ያገኘውን ያህል ይዞ ለመሄድ ለነገ ትኬት ቆርጧል፡፡ ሳገኘው ያንኑ ከልኩ ያለፈ ኮት ለብሶ በፈገግታ ተቀበለኝ፡፡

ስለ ወንጌልና ብርሃን እንደ ቤተሰብ በጉጉትና በሩጫ መጥተው ሲጠመጠሙብኝ እምባዬ ተናነቀኝ፡፡

‹‹ይሁን ለአንተና ለቀጣይ አገልግሎትህ የሚሆን የገንዘብ ስጦታ አዘጋጅቻለሁ›› አልኩት፤ ገቢ አሳድጅነቴ ቀርቶ ሰጭነትን በመጀመሬ እየተደሰትኩ፡፡

ይሁን ወደ መሬት አቀረቀረ የእምባ ዘለላዎች ከአይኖቹ እየረገፉ መሬቱን ያርሱ ጀመር፡፡ እኔም የእርሱ የውስጥ ምክንያት ባይገባኝም አብሬው አለቀስኩ፡፡

‹‹በተቃዋሚዎች የድንጋይ ናዳ የተበሳሳው የቤተ ክርስቲያኒቱ ጣራ ዝናብ ጠብ ካለ መቀመጫ ያሳጣናል፣ ችግረኛ ወገኖችም የየዕለት የእምባ ጸሎት ምክንያቶቻችን ናቸው፡፡ ለወንጌል ሰባኪዎች መንቀሳቀሻ የሚሆን ሞተር ሳይክል ፈልገንም ጸልየን ነበር፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰማ!›› አለ በሲቃ በታጀበ ድምጽ፡፡

አሁንም ይሄ ሰው ሐሳቡ ስለ ወንጌል ነው፤ እኔም ከራሴ ሩጫ መውጣት መጀመሬን ማሰብ ጀመርኩ ስለ ወንጌልንና ብርሃንን በትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ወጭያቸውንና የአመት ልብሳቸውን እንደምሸፍን በሕይወት እስካለሁና እነርሱ ትምህርት እስኪጨርሱ ከጎናቸው እንደምቆም ነግሬያቸው አብሬያቸው ፎቶ ከተነሳሁ በኋላ ተለያየን፡፡

አሁን ቤቴ ገብቼ ጣሪያዬን ሳይ ‹‹ስለ ወንጌል ያለብኝን ድርሻ ለመወጣት ጉዞ ጀምሬያለሁ›› የሚል ደብዘዝ ያለ ጽሑፍ ያነበብኩ መሰለኝ፡፡ በሞባይሌ ላይ ያሉትን ፎቶዎች ስመለከት በፈገግታ አቅፋኝ የተነሳቸው ስለ ወንጌል ስለ ወንጌል በቤተሰቦቿ ምክንያት የሚያልፍባትን መከራ ለመቀነስ አብሬት እንዳለሁ አሰብኩና ስለ ወንጌል የሚለውን ክፍል አውጥቼ አነብኩት፡፡

‹‹በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።›› 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡23-24

አንተስ አንቺስ ስለ ወንጌል ምን አደረጋችሁ? ሌሎች ስለ ወንጌል ነፍሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ደስታቸውን፣ ተድላቸውን፣ አካላቸውን ደግሞም ያላቸውን ሁሉ እየሰጡ ነው፡፡ ሁሉን መስጠት ቢቻል ታላቅ ክብር ነው፣ ነፍስን የመስጠት እድል ለጥቂቶች የተሰጠ ነው፣ ሀብትን መስጠት ጌታ ኢየሱስን የመምሰል ምልክት ነው፤ አስኪ ስለ ወንጌል ብለን የሆንነውን እናስብ?

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *