ፈጣኑ አሣሄል – በዶ/ር እዮብ ማሞ

ፈጣኑ አሣሄል – በዶ/ር እዮብ ማሞ

ዘመኑ ይሁዳ ዳዊትን፣ እስራኤል ደግሞ ሳኦልን የተከተለበት ዘመን ነበር። በሁለቱ ቤቶች ውግያ ንጉሥ ሳኦል ሞቷል። በዚህ ዘመን ነበር አሣሄል የተባለ ፈጣን ሰው ከወንድሞቹ መሃከል በገባኦን ጦር ሜዳ ላይ የተገኘው። የዚህን ሰው እጅግ ፈጣንነቱን ሁለተኛ ሳሙኤል ሲገልጠው፣”አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ” ይለዋል (2ተኛሳሙ 2:18)። ይህ ፈጣን ሰው አበኔር የተባለው ሃያል የሳኦል ጦረኛ ከሰልፍ በሚያመልጥበት ጊዜ በፍጥነት ደርሶበት ያሳድደው ጀመር። አሣሄል ይህን ታዋቂና የተወደደ የሳኦል ጦር ጄነራል አባሮ መያዝን እንደ ትልቅ ምርኮ ያየው ይመስላል። የሚያስገርመው ነገር ፈጣኑ አሣሄል በእጁ መሳርያ እንኳን ሳይይዝ ነበር ጦረኛው አቤኔርን የሚያሳድደው። ብዙም ሳይቆይ አሳዳጁ አሣሄል በአቤኔር ጦር ተወግቶ ሞተ።

አለማስተዋሉና ያየውን ነገር ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የማሳደዱን ነገር ስንመለከት አሣሄል ከዳዊት ሰዎች መካከል ያለም አይመስልም። ዳዊት ራሱ የሚታወቀው አንድን ነገር ለማድረግ ከመውጣቱ በፊት፣ ”ልውጣን?” ብሎ ከእግዚአብሄር ጥበብን በመጠየቅ ነው።

በዛሬው የምናቀርብላችሁ ጽሁፍ ውስጥ ምናልባት ይህ የእኛ ትውልድ የአሣሄልን አካሄድ የለመደ ትውልድ ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ተገደናል። አንድ ነገር ስለተገኘ ብቻ ለመከታተል በጣም የፈጠነ ትውልድ እያየን ነው። ወገኖቼ :- ምርኮ፣ ስኬት፣ መባረክ፣ መብዛት፣ መትረፍረፍ፣ መወደድ፣ መበልጸግ፣ መታወቅ፣ የበር መከፈትና የመሳሰሉት መልካም በረከቶች ናቸው። ሆኖም በጭፍንነት፣ ባለማስተዋልና በእግዚአብሔር የጦር ዕቃዎች ሳንሸፈን ከተከተልናቸው ግን ልባችንን የመወጋት አደጋ ያስከትላሉ። እግዚአብሔርን ይዘን ብንይዛቸው ችግር የለበትም። በፊታችን ያየነውን ነገር መከታተላችንም በራሱ ክፉ አይደለም፣ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ለመያዝ ስንሮጥ የጌታንና የህይወታችንን ዋና ጉዳይ ችላ ካልን ግን ትልቅ ችግር ውስጥ እንገባለን። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ከፈጣኑ አሣሄል ታሪክ በመነሳት እንመልከት:

  1. የምንወደውን ሰው በፍቅር ለመያዝ መከታተል መልካም በረከት ነው። አንዳንዶች ይህን በረከት በቶሎ ለማግኘት በጣም ፈጣኖች ናቸው። መለስ ብሎ ቢወጋቸው እንኳን የሚከላከሉበትን የጦር እቃቸውን ጥለው እስከመከተል ይደርሳሉ። የማባረሩ አባዜ ሲለውጣቸው፣ ከጸሎት፣ ከቃሉ፣ ጌታን ከመፍራት፣ ከማገልገልና ከቤተክርስትያን አምልኮ ሲያጎድላቸው ልባቸውን ለመወጋት እያዘጋጁ መሆናቸውን ይረሳሉ።
  2. ቢዝነስ ወይም ንግድ ሲያተርፍና ሲያድግ ማየት እጅግ ያጉዋጓል፣ ታላቅና ብዙዎች ለመያዝ የሚሮጡለት በረከት ነው። ሆኖም በሩጫና በፍጥነት በንግድ ዓለም ውስጥ ጭልጥ ብለን ስንገባ እና ማንነታችን ሲለወጥ፣ ከጸሎት፣ ከቃሉ፣ ጌታን ከመፍራት፣ ከማገልገልና ከአምልኮ ሲያጎድለን ጠላት አገኘን ማለት ነው።

ትምህርት፣ መማር፣ መሻሻል፣ እውቀት ማግኘትና በድግሪዎች መታጀብ ሰው ሁሉ ሊከተለው የሚገባ መልካም ነገር ነው። ለዚህ ምድር ብቻ የሚጠቅመው የአእምሮ ትምህርት ግን ለዘላለም ከሚጠቅመው የእግዚአብሔር ነገር ሲያጎድለን ለጠላት ጦር ያጋልጠናልና እንጠንቀቅ።

የአሣሄል ስህተቶች

1 አሣሄል ፍጥነት ስለነበረው ብቻ ነበር የተከተለው። የምንከታተለው ማንን፣ ምንና እና ለምን እንደሆነ ሳናውቅ ችሎታው፣ ፍጥነቱና ቅልጥፍናው ብቻ ስለአለን አንድን ነገር መከተል ያስወጋል።

2 አሣሄል ብቻውን ነበር። በረከታችን ከሕብረት አሰራር ሲነጥለንና ብቻችንን ገለል እንድንል ሲያደርገን ጠላት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያገኝን እያሰበ መሆኑን አንዘንጋ።

3 አሣሄል መሳርያና መከላከያ አልያዘም፦ የምንከታተለው ማንኛውም ነገር ምንም መልካም ነገር ቢሆን ልባችንን ካልጠበቅን ልንጎዳበት እንደምንችል አንዘንጋ።

4 አሣሄል ጥበብ አልነበረውም። መሮጡን፣ መፍጠኑን፣ ለመውረስ መጉዋጓቱን እንጂ ካለእውቀት እና ጥበብ ሲሮጥ ልውረስ ባለው ነገር ሊወረስና ሊመታ እንደሚችል አላስተዋለም። ሩጫ እንጂ እውቀትና ጥበብ አናይበትም። እውቀት(KNOWLEDGE) ምን ማድረግ ጥበብ(WISDOM) ደግሞ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ያሳየናል።

በአሣሄል ተመሳሳይ ስህተት ላይ እንዳንወድቅ ቅዱሳን በብዙ ነገሮች ከምናባርራቸው ወይም በጉጉት ከምንከተላቸው ነገሮች መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ምርኮና በረከት የመሰሉንን ነገሮች በቶሎና በሩጫ ለማግኘት ሲሉ ብዙዎች ይታለላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የመቀደምና ሁዋላ የመቅረት ስሜት ሳያስቡት እያስሮጣቸው ወድቀዋል።

እናስተውል! ትምህርት መማር ከቃሉ ትምህርት እና ከቅዱሳን ሕብረት ከለየን፣ ነግዶ ማትረፍ ማትረፍያ ከሆነው እግዚአብሔርን ከመምሰል ሕይወት ካጠፋን፣ ፍቅረኛ ማግኘት ከክርስቶስ ፍቅር ከለየን፣ የተሻለ ኑሮ በመንፈሳዊ ሕይወት ከማደግ ከለየን እጅግ አደገኛ ነው። ጠንቀቅ ማለትም ያንጊዜ ነው።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ጸጋ ይብዛላችሁ!

ከ www.Tsega.com ላይ ከአለው የሰሊሆም መጽሔት በፍቃድ የተወሰደ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *