የ “ታላቁ ሩጫ” የምረቃ ስነ ስርዓት

የ “ታላቁ ሩጫ”   የምረቃ ስነ ስርዓት

“ታላቁ ሩጫ” በሚል ርእስ የወጣው የደራሲ ዓለማየሁ ማሞ አስራ ሁለተኛው መጽሐፍ ቅዳሜ ኦክቶበር 31 ቀን በርካታ ደራስያንና ስነ ጽሁፍ ወዳድ ታዳሚዎች በተገኙበት ተመርቆ ለስርጭት ቀርቧል። ስፍራው ሃያትስቪል ሜሪላንድ በመለኮት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን አዳራሽ ነበር።:

ፕሮግራሙ በሰዓቱ መጀመሩ ለደራሲ ዓለማየሁ ማሞ የመጽሐፍ ምረቃ ዝግጅቶች አንዱ መለያ ሆኖለታል። የደራሲውን ሰዓት አክባሪነት በማየት ስለመጽሐፉ እንድንናገር  የተጋበዝነው አብዛኛዎቻችን ተወስኖ በተሰጠን አስር ደቂቃ ውስጥ እጥር ምጥን ያለና በመንፈሳዊ ቅኔ የተቀመመ ንግግር አቅርበን መቀመጣችን ለፕሮግራሙ ውበት ነበር:: ይህ እጥር ምጥን የሚባል ነገር እንደምታውቁት ሰባኪዎቻችንን አይጨምርም:: የእነሱ ሰዓት ውስጣቸው ባለው እሳት ይመስለኛል:: እሳቱ ካልቀዘቀዘ መድረኩን በሰዓት የሚያስለቅቃቸው የለም:: እናም የፕሮግራሙ የመዝጊያው ስነ ስርዓት በጥቂቱም ቢሆን የዘገየበትን ምክንያት ልግለጽላችሁ ብዬ ነው::

ለስነ ጽሁፍ አክብሮት ያላቸው ክርስትያን ደራሲዎች ጸሐፊዎችና አንባብያን የሚሰበሰቡበት ጉባኤ በዚህ አካባቢ እምብዛም አልተለመደም::  ሆኖም በዕለቱ ያገኘሁዋቸው በርካታ ደራስያን እና ጸሐፊዎች ግን ለዚህ ዓይነት ስብሰባ ያላቸውን ናፍቆት ለመመልከት ችያለሁ:: አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች የሚናገሩትና የሚጨዋወቱት ነገር ለብዙዎች ሊካፈል የሚገባ መንፈሳዊ ቅኔ ነበረው። ንግግራቸው በጸጋ የተቀመመና አብራችሁዋቸው ብትውሉ እንኳን የማይሰለች ሲሆን ከተለምዶው የጴንጤ ጭውውትም የዘለለ ነው። ለንግግራቸው ዋቢ ከቅዱሳት መጽሐፍት ወይም ከአነበቡበት ሰው ጽሁፍ ይጠቅሳሉ። ንግግራቸው ውስጣችሁን ይጠይቃል። ለጥያቄያችሁ መልስም ወደ ቅዱሳት መጽሐፍት መሄድ ግድ ይላችኋል።  ይህ የተረሳውን የጥንቷን የእናት ቤተ ክርስትያንን የቅኔ ጉባኤ አስታወሰኝ።  መርስዔ ሃዘን ወልደቆርቂስ የተባሉት ታላቅ ታሪክ ጸሐፊ በቅርብ በወጣው መጽሐፋቸው ሲጠቅሱ “ታላላቅ የቅኔ ጉባኤዎች በቤተመንግስት እና በታላላቅ ገዳማት ውስጥ እየተዘረጉ የብዙ ሊቃውንት መንፈሳዊ ቅኔ በአድናቆት ይደመጥ ነበር” በማለት ጽፈዋል::

ይህን አይነት የመንፈሳዊ ቅኔና የስነ ጽሑፍ ጉባኤ ጅማሬ በታላቁ ሩጫ መጽሐፍ ምረቃ ላይ ለማየት ችያለሁ::  “ታላቁ ሩጫ” የሚለው የመጽሐፉ ርዕስ ሳይቀር ሰምና ወርቅ ያለው ነበር:: በተለይ የክብር ተናጋሪ ሆኖ ከቦስተን የመጣው ታዋቂው የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት የነበረው የበላይነህ ዲንሳሞ መገኘት መጽሐፉን ስለ ማራቶን ሩጫ ሊያስመስለው ይችላል።  “ታላቁ ሩጫ” መጽሐፍ ግን ስለሌላ የተጠራንበት ታላቅ ሩጫ ነበር:: ለዓመታት የታላቁ የማራቶን ሩጫ ክብረወሰን ባለቤት የነበረው በላይነህ ዲንሳሞም የክብር ሽልማቱ ታላቅ የሆነ ሌላ ታላቅ ሩጫ እየሮጠ መሆኑን ነበር በንግግሩ ያበሰረን። የክብር ሽልማቴን ከእጁ እረከባለሁ የሚለን በላይነህ ዲንሳሞ በቦስተን ቤተክርስትያን በሽማግሌነት እያገለገለ ይገኛል:: ስለጀመረው ሩጫም ሲገልጽ የአሁኑን ሩጫውን ለየት የሚያደርገው ታላቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እና ሩጫውን አቁዋርጦ መውጣት ያለውን አደጋ በመግለጽ ምክሩን በስፍራው ለተገኙነው ለግሶናል። በመቀጠልም በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአለፉት አስርት ዓመታት የሮጣቸውን እና አሁን የሚሮጠውን ሩጫ ታሪኮች በመንፈሳዊ ቅኔ ቀምሞ በመጽሐፍ እንደሚያቀርብ ለጸጋ የመጽሔት አገልግሎት ቃል ገብቶልናል።

የደራሲ ዓለማየሁ ማሞ መጽሐፍት አስራ ሁለት ወይም አንድ ደርዘን ሞልተዋል:: ትውልዱን የሚመለከትበት ልዩ መነጽር ያለው ደራሲና ጋዜጠኛው ዓለማየሁ ዛሬ በርካታ ቅዱሳንን በውስጣቸው ያለውን ጸጋ እያበረታታ መጽሐፍ እንዲጽፉ እያገዘ ነው:: “ጸጋ የመጽሔት አገልግሎት” ለደራሲው ያለንን አድናቆት እየገለጽን ጌታ እየሱስ ጸጋውን ያብዛልህ ለማለት እንወዳለን።

የደራሲ ዓለማየሁ ማሞን አስራ ሁለት መጽሃፍት ለመግዛት የምትፈልጉ የ ጸጋን ድረ ገጽ www.Tsega.com ን ይጎብኙ።

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *