የመምህር ጽጌ “ይነጋል” ውይይት ተካሄደበት

የመምህር ጽጌ “ይነጋል” ውይይት ተካሄደበት

Hintset.org – Addis Ababa Ethiopia,
በሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አዘጋጅነት በየወሩ የሚካሄደው ሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ እሑድ መስከረም 8 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ተካሄደ፡፡ በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት አዳራሽ በተከናወነው መርኀ ግብር፣ ለውይይት የቀረበው መጽሐፍ “ይነጋል” የተሰኘውና በዲያቆን ጽጌ ሥጦታው የተጻፈው መጽሐፍ ሲሆን፣ የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ቀሲስ ሰሎሞን ደረጀ ናቸው፡፡

መጽሐፉ፣ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፥ በሊቃውንት ጕባኤውና በዲያቆን ጽጌ ሥጦታው መካከል የተደረገ የሃይማኖት ክርክር (ውይይት)” ሲሆን፣ ክርክሩ/ውይይቱ የተካሄደው በ1990 ዓ.ም. ነበር፡፡ ክርክሩ ከተካሄደ ከ7 ዓመት በኋላ ለንባብ የቀረበውን መጽሐፍ ያሄሱት ቀሲስ ሰሎሞን በበኩላቸው፣ “ይነጋል” የተሰኘው መጽሐፍ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ከገለጹ በኋላ ጎድሎታል ያሉትንና ባይከታት በሚል ያነሷቸውን ትችቶች አስደምጠዋል፡፡ በተለይም፣ ጸሐፊው በሊቃውንት ጕባኤውና በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ሰንዝረውታል የተባለው የጠነከረ ትችት አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ጊዜ የወስደ ውይይት ተደርጓል፡፡

ጸሐፊው ዲያቆን ጽጌ በበኩላቸው፣ በመጽሐፋቸው ያቀረቡት ጠንከር ያለ ትችት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፣ ይህንንም ማድረግ ያስፈለገው ክርክሩ/ውይይቱ ምን ይመስል እንደ ነበረ ለአንባብያን ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሆኑና ታሪካዊ ፋይዳውን ለማጉላት በመፈለጋቸው እንደ ሆነ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም፣ መጽሐፋቸው በዚህ መልኩ መቅረቡ ካስከተለው ጉዳት ይልቅ ያመጣው ጥቅም የሚበልጥ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡

በመጪው ጥቅምት 6 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. ውይይት እንዲካሄድበት ቀጠሮ የተያዘለት “የፍሬሿ ማስታወሻ” የተሰኘው የሔርሜላ ሰሎሞን መጽሐፍ ነው፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *