ወቅታዊ የስህተት ትምህርቶች – ስሜ ታደሰ

ወቅታዊ የስህተት ትምህርቶች – ስሜ ታደሰ

ከስሜ ታደሰ እና ከዘላለም መንግስቱ ጽሑፎች  ተወስዶ ለቤርያ የቴሌኮንፍረንስ የአየር ስርጭት በኮነ ፍሥሐ የተዘጋጀ። በድምጽ ለመስማት ዘወትር ቅዳሜ ከጠዋቱ 3 ሰዓት EST ላይ በስልክ ቁጥር 1+712 432-5222 CODE# 2484446 ይደውሉ።

ከ30 ዓመታት በፊት ‹ትምህርት ለምኔ›› በሚል እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ወንድሞችና እህቶች ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው ‹‹ጌታ ብቻ›› በማለት ‹‹ለአገልግሎት›› ወጥተው ታይተዋል፤ እነርሱም ዓለማዊ የመሰሉ ነገሮችን ሁሉ በመናቅ በፆም በፀሎት፣ በዝማሬና በሕብረት በመሆን ከዓለም ተገልለው ቆይተዋል። ይህን የመሰለው ውሳኔ የመጣው ግን ባግባቡ ቅዱሳት መጽሐፍትን ባለመረዳትና ስሜታዊ በመሆን የመጣ ነበር›› እንደ እውነቱ ከሆነ የተሳሳቱ አገልጋዮች በመማር ላይ ያሉትን ለተሳሳተ ውሳኔ አድርሰዋቸው ይሆናል፤ አልያም ጊዜን ማባከን ዕድሜን ለከንቱ ተግባር መሸጥ ነው በሚል የሰማዩን ቅድሚያ ለመስጠት ተበረታተው ተደራጅተው ይሆናል፤ ምንም ይሁን ምን በተለያየ ሁኔታ ምክንያት ሰዎች በእግዚአብሔር ስም፣ ከትምህርታቸው፣ ከስራቸው ተለይተው ወጥተዋል።

እኔ እንደማውቀው እነዚህ ከ30 ዓመታት በፊት በሐዋሳ የተግባረ እድ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ አማኞች ‹‹ከተገለጠላቸው መገለጥ›› የተነሳ የደርግ መንግስት ባለ ስልጣናትን አውርደው ስፍራውን የሚይዙበት ቀን ተጠባብቀው ነበር፤ በፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ በፍቅረ ስላሴ ወግደረስ፣ በፍስሐ ደስታ እና በብርሀኑ ባዩ ቦታዎች ሁሉ አማኞች በስም ተሰይመው ነበር። (ምንጭ በወቅቱ ተሳታፊ ከነበረው ታደለ ሀ/ኢየሱስ ኑዋሪነቱ በአሜሪካ) ይህ አይነት እንቅስቃሴ የመጣው ምናልባት ክርስትና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርስ መንግስት እስከ መቼ ይኖራል? በሚል መነቃቃት ሊሆን ይችላል፤ አልያም በጊዜው ባልተፈተሹ መገለጦች ከመፅናት የተነሳ ይሆናል፤ ያሉት ግን አልሆነም ደርግን ያንበረከከው ሌላ ከሰሜን የመጣ ጦር ነበር፤ ከዚያም ዘግይቶም ቢሆን መንግስቱ በወንጌላውያን አልተያዘም።

እኒህን የመሰሉ አንድ አቅጣጫን ወይም ፊት ለፊትን ብቻ አመላካች የሆኑ የጋሪ ፈረስ እይታዎች ግራ ቀኙን ባለማስተዋል ሊከሰቱ ሊፈጠሩ ይችላሉ።  እንደ እውነቱ ከሆነ የተሳሳቱ ትምህርቶችና ግንዛቤዎች መነሻቸው ለየቅል ነው፤ መለሰ ወጉ በ2005 ባሳተመው ‹‹ካርቦን ኮፒ ክርስትና›› ላይ ‹‹ያልሆነውን ሆነን ከምንወደድ የሆንነውን ሆነን ብንጠላ ይሻላል›› ይላል፤ ይህም የየትኞቹም ወይም የአብዛኞቹ ተሳሳች ግንዛቤዎች መነሻቸውን ያደረጉት በ‹‹እንደወረደ ተቀበለው›› እንቅስቃሴ ነው።

በአንድ ወቅት አንድ የታወቁ አገልጋይ በፃፋቸው መጽሐፍትና በሰበኩት ስብከት አጋንንነት በአማኝ ውስጥ ይገባል፤ ካሉ በኋላ መውጪያው ትውከትና ተቅማጥ ነው ብለው ሰበኩ፤ ይህን እንደወረደ የተቀበለው ማህበረሰብ ሰውየው በመሰለው ያስተማረውን ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ነው›› ብሎ ፀናበት ኋላ ኋላ ግን ሰውየው ‹‹ተሳስቻለሁ›› ብሎም ንስሀ ገባ፤ የእሱ ንስሀ ግን ትምህርቱን ለተቀበሉት ለመላው አዳምና ሔዋን ባለመድረሱ ዛሬም የሰውዬውን ተሳስቼአለሁ ያልሰሙና በልምምድ የሚንገታገቱ አማኞች አሉ፤ ‹‹ምክሮ አስሞካሬ›› ማለት ይህ ነው።

እንደ ወንድም ዶ/ር መለሰ ወጉ አገላለፅ ‹‹እኛ ሰዎች እርስ በርሳችን የምንመሳሰልባቸው ነገሮች አሉን፤ የተፈጠርነው በእግዚአብሔር አምሳል ነው፤ ሁላችን ማሰብ፣ ሀሳባችንን በንግግር መግለፅ እና ማገናዘብ እንችላለን፤ ሁላችን የራሳችን የሆነ ስሜት፣ የራሳችን የሆነ ፈቃድ አለን፤ ደስ ሲለን እንስቃለን የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመን እናለቅሳለን እንዲህም ቢሆን ግን አንድ አይነት የሆኑ ሁለት ሰዎች በዓለም ላይ የሉም… (ፎቶ ኮፒ ገፅ 16-17) ።  ካርቦን ኮፒ መጽሐፍ ዳዊትን በመረጃነት ያቀርባል ‹‹ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ሲቀርብ አስደንጋጭ የሆነ የወታደር መልክ ስላልነበረው የዳዊትን መልክ ለመለወጥ ሳኦል የራሱን ዕቃ ጦር አለበሰው፤ ይሁን እንጂ አውልቆ የአባቱን በግ ሲጠብቅ የሚለብሰውን የራሱን ልብስ ለበሰ፤ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ሲቀርብ ወታደር ሆኖ ሳይሆን በግ ጠባቂ ሆኖ ነው፤ ሳኦል የሞከረው ዳዊትን ወታደር ለማድረግ ሳይሆን ወታደር እንዲመስል ነበር…›› (ካርቦን ኮፒ… ገፅ 28)  :: ዳዊት ራሱን ሆኖ መቅረቡ ግን ለማሸነፍ አስተዋፅኦ ኖረው፤ የተሳሳተ ትምህርት እና አደራረግ ራሳችንን ካለማወቅ ከራሳችን ጀምሮ ይስፋፋል።
የካርቦን ኮፒ ክርስትና መጽሐፍ ፡- ‹‹አንዱ ካመነ እነርሱም ያምናሉ።
– አንዱ ሲፀልይ ካለቀሰ ማልቀስ ደንብ ይመስላቸውና ያለቅሳሉ
– አንዱ ከሳቀ እነርሱም ይስቃሉ
እንዲህ በሆነበት ቦታ ሁሉ የተሳሳተ ትምህርት ተግባራዊ አቅምና ጉልበት ያገኛል።

በካርቦን ኮፒ መጽሐፍ ውስጥ ቶማስ በጥሩ ምሳሌነት ተጠቅሷል። ቶማስ የፎቶ ኮፒ ሕይወትን እንዳልመራ ይልቅኑ ራሱን ሆኖ እንደዘለቀ በማረጋገጥ ተጠራጣሪ ሳይሆን እውነትንና እርግጠኛ አቋምን ለመያዝ ይተጋ እንደነበር እንደሚከተለው ያብራራል (ፎቶ ኮፒ ገፅ 37)
አንዱ፡- ኢየሱስ ስራዬን ጨርሼ በምድር አከበርኩ ባለበት ወቅት ለደቀመዛሙርቱ እንደሚለያቸው ነግሮአቸው ነበር፤ ቶማስ ግን ‹‹ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?›› አለው (ዮሐ 14፡5) ጥያቄው ተገቢ ምላሽን ለራሱ አገኘ፤ ምላሹም ለ2000 ዓመታት በምድር ላይ ላለችው ቤተ ክርስቲያን መሰረት ሆኖ ዘለቀ ‹‹እኔ መንገድ፣ እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚደርስ ማንም የለም›› (ዮሐ 14፡6)ን አስገኘ፤ ይህን መሰረታዊ ምላሽ ከተቀሩት 11 ደቀመዛሙርት ጥያቂ ተነስቶ የመጣ አልነበረም። ከቶማስ እንጂ።
ሁለተኛው፡-በአገልግሎት ዘመኑ ኢየሱስ የሚወዱት ወንድማቸው ከሞተበት ከአላዛር መካነ መቃብር ተገኝቶ ወንድማቸውን ከሞት ማስነሳቱ ይታወቃል (ዮሐ. 11) ይህ ስራው ጠላቶችን አብዝቶበት እሱን ለመግደል መታደኑን ቃሉ ይተርክልናል፤ ይህ አድማ ወደተጠነሰሰበት ስፍራ ኢየሱስ አስቀድሞ ለመሄድ ወሰነ፤ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሚያደርገውን አያውቁም፤ ቶማስ ግን ከዚህ ቀድሞ በጌታ ኢየሱስ ላይ የተሞከረውን ውዝግብና ዛቻ ያውቃልና ‹‹እንሂድ›› ባላቸው ጊዜ ‹‹መምህር ሆይ አይሁዳውያን ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር ታዲያ እንደገና ወደዚያ ተመልሰህ ትሄዳለህ?›› አሉት (ዮሐ 11፡8) ምላሹ ‹‹አልአዛርን ከእንቅልፍ ልቀሰቅስ መሄድ አለብኝ›› አላቸው እነርሱ ግን አልገባቸውም ይልቅኑ ወደ ይሁዳ መመለስን ሁሉም አልፈለጉም፤ በዚህ ሰዓት ነበር ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት ‹‹ከእርሱ ጋር እንድንሞት እኛም እንሂድ›› ያላቸው (ዮሐ. 11፡16) ይህ ቃሉ በብዙዎች ተስፋ የቆረጠ ቃል ይመስላቸዋል ግን አይደለም፤ የቁርጠኝነት ውሳኔ ነው፤ ‹‹ኢየሱስ የሚሞት ከሆነ ብቻውን መሞት የለበትም እኛም ልንተባበር ይገባል›› ነበር ቶማስ ያለው።
ሶስተኛው፡- የቶማስ ጥንካሬ የኢየሱስን ትንሳኤ በደቀ መዛሙርቱ አረጋግጠው በጊዜው ላልነበረው ቶማስ ኢየሱስ መነሳቱን አብስረውለት ነበር። ቶማስ ግን ይህን አልተቀበለም፤ አለመቀበሉ ላለማመን ፈልጎ ሳይሆን እርግጠኛ ሆኖ ለመዝለቅ እና ቀጣዩን ሕይወቱን በአግባቡ ለመምራት ፍላጎት ስላደረበት ‹‹ጌታን እኮ አየነው›› ‹‹ከሞት ተነስቷል ጌታችን›› ብለው ቢቦርቁም እሱ ግን ‹‹በምስማር የተወጋውን እጆቹን ካላየሁና ጣቴን ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ቁስል ካላገባሁ አላምንም›› ነበር ያለው፤ (ዮሐ. 20) ኢየሱስም ይህን ጥያቄውን አላቃለለውም፤ በመጠየቁም አልነቀፈውም ይልቅስ ‹ጣትህን ወዲህ አምጣ እጆቼን እይ አለው (ዮሐ 20፡27) ቶማስ ሌሎች ያደረጉትን የሚያደርግ፣ የሰማውን የሚደግም በቀቀን አይደለም፤ ይመረምራል፤ ይጠይቃል፤ እርግጡንም በማግኘት ይረካል።
የስህተት ትምህርቶች የማይጠይቁ ማህበር በበዙበት ይስፋፋል፤ ቶማሶች በሌሉበት ስፍራ ሁሉ ግርግርና መናፍቅነት ይበዛል።
ዘላለም መንግስቱ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ እና የአፈታት ስህተቶች›› በሚል በ2000 ባሳተመው መጽሐፍ መናፍቃዊ አስተሳሰቦችንና የስህተት ትምህርቶችን ልብ ማለት የሚያስችሉ መረጃዎችን አቀብሏል።
‹‹የሐሰት ትምህርቶች አብዛኛው ሰውነታቸውን ከውኃ ውስጥ ደብቀው እንደሚንሳፈፉ አዞዎች ናቸው፤ እንዲህ ያሉ አዞዎች የመተንፈሻ ቀዳዳቸው ያለበትን የአፍንጫቸውን ክፍል ብቻ አውጥተው በወንዝ ላይ ይንሳፈፋሉ፤ አንዳንዱ የዱር እንስሳት ድንጋይ መስሎአቸው መጥፊያቸው መሆኑን ሳያስተውሉ ተረማምደው ሊሻገሩበት ይሞክራሉ፤ አንዳንዶቹ በትልቅ ጉዳት ሰውነታቸውን ያተርፋሉ፤ ብዙዎቹ ተይዘው ይበላሉ የስህተት ትምህርቶችን ባለማስተዋል መረማመጃ መስሎአቸው የረገጡና የተነከሱ፣ የተበሉ ብዙ ናቸው›› (መጽሐፍ ቅዱስ – ዘላለም – ገፅ 248)
የስህተት ትምህርቶች ስህተት መሆናቸውን ለማወቅ የሚያስችል ሁነኛ መገለጫ የላቸውም ይልቅኑ የሌሉ መስለው ይኖራሉ፤ ሲነቃባቸው በቀላሉ ያፈገፍጉና ይጠጋሉ፤ ለተዘናጋባቸው መጠቂያው ሆነው መንፈሳዊ ሕይወትን ያደክማሉ ያጠፋሉ።
የስህተት ትምህርቶች፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ ልከኛ አስተምህሮ ርቀው ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ ሰው አተኳሪ ትምህርቶች ናቸው፤ ለስልጣን ጥም ተገዢ፣ እኔን እዩኝ እኔን እዩኝ የሚል ዝንባሌ አላቸው።
ብዙውን ግዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለመንደርደሪያነት ብቻ ተጠቅመው የገዛ ማብራሪያቸውን በማጨቅ ያስተምራሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ክርስትና ግብ አለው እሱም ‹‹የልጁን መልክ በመምሰል መዝለቅ ነው›› ይህን ተቃራኒ የሆነ የትኛውም አጓጓዝ ከስህተት ትምህርት አንደኛው ቅርንጫፍ ነው። በአንዳንዶች ዘንድ ሰዎች በርካታ ልምምዶችና ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፤ በዚያም መንገድ ትልቁን መንፈሳዊ ድልድይ ተሻግረው ወደ መንፈሳዊ ዓለም እንደገቡ በማመን ይደላደላሉ። በትይዩ ያልተለማመዱትን ስጋውያን እንደሆኑ ያምኑባቸዋል፤ የግል ልምምድ የልዩነት መንስኤ ሆኖ ወገኖችን ይከፋፍላል፤ ይህ ሲሆን ወደ ክርስቶስ ቁመት ማደግ በቁልቁል ይተካል፤ ቁልቁሉን እንደ አደጉ እንደ መቁጠር መናፍቃዊ ትምህርት የለም። ዘላለም በአንድ ወቅት መጋቢው የሰጠውን ምሳሌ ያነሳል፤ ‹‹ልጅ አባቱን ብስክሌት እንዲገዛለት ለመነው፤ አባቱም እገዛልሀለሁ ይህም የሚሆነው አልጋህ ላይ ስትተኛ ከጫፍ እስከ ጫፍ በማደግ እርግጠኛ እሆናለሁ፤ እኔም ያኔ እገዛልሀለሁ›› አለው አባትየው ለአስራ አምስት ቀን ወደ ስራ ወጥቶ ሲመለስ ልጁ በደስታ ተጥለቅልቆ ‹‹አድጌያለሁ ግዛልኝ›› አለ፤ ከዚያም ማደጉን ለማረጋገጥ አባቱን ወደ መኝታው ክፍል ወሰደው፤ ከዚያም ራሱ እና የእግሩ ጫፍ የአልጋውን ሁለት ጫፍ እንደነኩ አሳየው፤ እውነትም ልጁ ከጫፍጫፍ ደርሷል ግን ልጁ የተጋደመው ከራስጌ ወደ ግርጌ ሳይሆን ከጎን ወደ ጎን ነበር (ዘላለም ገፅ 254)። ይህ ትንሽ ልጅ፡- ለራሱ በመሰለው መንገድ አድጓል፤ እርግጥም ከጫፍ ጫፍ ደርሷል፤ ይህ እድገት ግን የልጁን አእምሮአዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና አካላዊ እድገትን ያላከተተ ስለሆነ ዕድገቱ በጤነኛነቱ አይበሰርም። ብዙ የስህተት ትምህርቶች የሚጀምሩት የልጁን አይነት የእድገት አቋራጭ መንገድ በመጠቀም ነው፤ ይህ ደግሞ ክርስቶስን ወደ መምሰልና ወደ እርሱ ቁመቱ ስለማያመጣ ጥቅም የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ አቋራጮች ደርጅተው የሚወጡት ከክርስቲያኑ ማህበረሰብ ነው፤ ከቤተክርስቲያን፤ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መወዛገብ ፋይዳ የለውም ይልቅስ ‹‹ከመካከላችን ሊወጣ የመቻል አቅም ካለ ያ እንዳይፈጠር መትጋት ያስፈልጋል።
በተያያዥ የስህተት ትምህርቶች ልክ ለአይጦች እንደሚቀርብ መርዝ ነው፤ የአይጥ መርዝ ከ100/98ቱ እህል ነው፤ ከ100/2ቱ ብቻ ነው መርዙ እሱን የተመገበ አይጥም ሆነ ሰው መርዝ የለውም ባይ ነው፤ የተለመደው ምግብ ነው ይላሉ ግን በልተው ብዙም ሳይርቅ ሞቶ መገኘት ግድ ነው። የስህተት ትምህርትም መኖር የሚገባውን የሰው ልጅ ሊገድሉት ይችላሉ፤ መሞት አካላዊ ብቻ አይደለም፤ በስሜት መኮላሸት፣ በአካል መድቀቅ፣ በመንፈስ መድከም በአእምሮ መደንዘዝ የዚህ የመሞት ሁነኛ መገለጫዎች ናቸው።
ክርስቲያን ምን ጊዜም ራሱን ከመመልከት መጀመር አለበት፤ ኢየሱስ በማቴ 7፡1-20 ከስህተት ትምህርትና መምህራኑ ተጠበቁ ሲል ዋናው ምክንያቱ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ለመግለፅም ነው። በመሰረቱ የሀሰት ትምህርቶችን ሀሰተኛ የሚያስብላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር አለመጣጣማቸው ነው። ቅዱሳት መጽሐፍት ቤተክርስቲያን ቀጣይነት እንዲኖራት ያደርጋሉ፤ መጽሐፍቱ ክርስቲያኖችን ለእድገትና ለነፃነት ያበቃቸዋል፤ ጤናማ ትምህርት ባለበት ቤተሰብ፣ ሕብረተሰብና ሀገር ይጠበቃል፤ እውነቱን እያወቁ ‹‹ቸል›› የሚሉ ሰዎች እና የቤተክርስቲያን አባላት የውሎ አድሮ ትርፋቸው በቁም መሞት ነው። ዛሬ ቸልተኝነት በብዙዎች ዘንድ አለ ይህ ደግሞ አንድ ራስን ብቻ አይጎዳም ብዙዎችን መቀመቅ ያወርዳል።
ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ፡- በማድረግ ‹‹የአፈታት ስህተቶች›› መጽሐፍ… የጃፓንንና የአሜሪካንን ጦርነት ያስነብባል ጃፓን በ1941 በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኘውን ሐዋይ ከምትባለው የአሜሪካ ደሴት ላይ ከፍተኛ አደጋ አደረሰች፤ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ 6 የጦር አውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ 8 የጦር ተሸካሚ መርከቦችን፣ 183 ተዋጊ አውሮፕላኖችን 3000 ተዋጊዎችን አሜሪካን በሞት አጣች። ያሳጣቻት ጃፓን ዝግጅቷን አጠናቃ ለወረራ ስትነሳ የአሜሪካ ራዳሮች አመላክተው ነበር በጊዜው የነበረው አዛዥ ግን ‹‹አትጨነቁ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም›› የሚል መልስ ነበር የሰጠው። አሜሪካዊው አዛዥ ቸል ባይልና ባይዘናጋ ይህን ያህል ከፍተኛ ጉዳት ባልደረሰ። አደጋ እንደሚኖር ማሰብ ተገቢ ነው፤ ለዚያም ተዘጋጅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፤ አልያ ግን የማይታመን መንፈሳዊ ጥፋትን ከስህተት ትምህርት የተነሳ ማምጣት ይቻላል። በመሰረቱ የካፒቴኑን የሚስተካከል ጥፋት በአንድ ሰው ላይ ብቻ ቢሰራ አሁንም የጥፋቱ ልክ ተቀራራቢ ነው።

ሌላው የገዛ ቸልተኝነት ነው፤ የስህተት ትምህርቶች ጉዳያችንን ብቻ በማድመጥ ዙሪያ ገባውን እንዳናይ የመከልከል አቅም አላቸው። እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ከውሳኔው ጋር ወይም ከምሪቱ ጋር አለመተባበርም የዚሁ መገለጫ ነው።
በደቡብ አፍሪካ ናታል በሚባለው ግዛት ውስጥ በሚገኘው ‹የአዞ ወንዝ› እየተባለ በሚጠራው ስፍራ በመዋኘት ላይ ሳለ አንድ ሰው በድንገት በአዞ ተይዞ እግሩን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ቢያስለቅቅም አዞው ግን እጁን ያዘበት፤ ሰውየው አሁንም ጥረት በማድረግ በያዘው ሰንጢ ሊቆርጠው ሞከረ አልሆነለትም በመጨረሻ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነ፤ እጁን መቁረጥ እና በሰንጢው ቆርጦ ከአዞው አመለጠ፤ ባለ አንድ እጅ ሆኖ ለመኖር መወሰንን ያመጣው አደጋው ነው፤ ለአደጋው መከሰት ሰውየው ሙሉ ሐላፊነት አለበት፤ በአዞ ሰፈር ተገኝቷልና ግን ደግሞ በአዞው ተውጦ ከመቅረት እጁን ገብሮ መኖር የተሻለው ውሳኔ ነው።
የስህተት ትምህርቶች ጉዳት ከማድረስ ወደ ኋላ አይሉም፤ እነርሱ ዘንድ በመሄድ ፈተና ውስጥ ከመውደቅ ውጤታማ የሆነ ሕይወት ለመኖር ተገቢውን ማድረግ ግድ ነው። ብዙዎች በክርስትና ስም በውድቀት፣ በጭንቀት፣ በቤተሰባዊና ማህበራዊ የሕይወት ቀውስ ውስጥ አሉ። ይህ እንዳይፈጠር ከወዲሁ መስራት መቻል የክርስቲያን ሐላፊነት ነው።

2 comments

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *