ከመቃብር የወጣው ሰባኪ – ከወንድዬ ዓሊ ጽሑፎች

ከመቃብር የወጣው ሰባኪ – ከወንድዬ  ዓሊ ጽሑፎች

ይህ ጽሑፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ሆነው ወንጌልን በመንፈስ ቅዱስ ሀይል ስላስፋፉት ቀደምት ሰማዕታት በወንድዬ ዓሊ ከተጻፈው የእኩለ ሌሊት ወገግታ ከሚለው ጽሑፍ ተወስዶ ለቤርያ የቴሌ ኮንፍረንስ አድማጮች የቀረበ ነው:: የጽሑፉ ርዕስ “ከመቃብር የወጣው ሰባኪ” ይላል።

ከ1940 እስከ 1966 በታሪክ ፊት ታሪክ የሌላቸው ምስኪን ገበሬዎች፣ ለዓይን የማይሞሉና የተናቁ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ሲራራ ነጋዴዎች፣የባላባት ወገኖች፣ ገባሮች፣ ጪሰኞች ከእግዚአብሔር ጋር ተስማምተው ስለሠሩ የሕዝብን ታሪክ ቀይሰዋል። በዓለም አቀፍ የወንጌል ስርጭት ተርታ ቢመዘን ከሐዋርያት ዘመን በስተቀር አምሳያ የሌለው በሌላ የተወሰነ ጊዜና ቦታ ያልተፈጸመ አድራጎት በመንፈስ ቅዱስ ኅይል ፈጽመዋል።

የክርስቶስን ወንጌል በደቡብ ኢትዮጵያ በማወጅ ረገድ አባቶች በጊዜውም ያለጊዜውም፣ በስፍራቸውም ያለስፍራቸውም በአስገራሚ ሁኔታ ተወጥተውታል። እስቲ በዘመኑ በልዩ መጎብኘት እግዚአብሔር የሰራውን ታሪክ እንመልከት።

በአእምሮአችሁና በልባችሁ የ1935 ዓ ም ጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛትን መልክ አስቡልኝ። በተለይ ደግሞ ኡሞ እና ኦቾሎ የተባሉ ሁለት ቀበሌዎችን ያዙልኝ። እንደዛሬው የእርሻ መሬት ሁሉ ለልማት ተብሎ ከመመንጠሩ በፊት ከኡሞ እስከ ኦቾሎ ለመድረስ ስምንት ሰዓት ያህል በእግር መጓዝ ያስፈልጋል።

በእነዚህ ሁለት ቀበሌዎች አማካይ መንገድ ላይ ወይዘሮ አለቄ የተባሉ መበለትና ሁለት ሕፃናት ልጆቻቸው ይኖራሉ። ወይዘሮ አለቄ ከልጅነት ባላቸው የወለዷቸው ወንዶች ልጆች በተከታታይ ስለሞቱባቸው ሃዘን ያጠቃቸው ሰው ነበሩ። በመጨረሻም የተወለደላቸውም ህፃን እንደቀደምቱ በለጋው እንዳይቀጠፍባቸው ሞት ይጠየፈዋል ብለው ያሰቡትን አስቀያሚ ስም አወጡለት። ጌለሾ አሉት ትርጓሜውም ዝንጀሮ ማለት ነው። ደርበውም ይቅርባችሁ የሚል ሌላ ስም ጨምረው አወጡለት። የሞት መልዓክም ተጭበረበረ፣ሳይነካውም አለፈ፣ ስምንት ዓመትም ሞላው።

በልጅ የተፈራው የሞት መልዓክ ግን ቀስቱን ወደ ባላቸው አዞረና ነደፋቸው። የወይዘሮ አለቄ ባል ሞቱ። ወይዘሮ አለቄም በከፍተኛ ሓዘን ተመቱ። ሌት ተቀን ማንባት ጀመሩ።እንባ የሸረሸረው ዓይን በቀላሉ ለበሽታ ተጋለጠ፣ ቀስ በቀስ ብርሃንና ጨለማ መለየት አቅቷቸው ቤት ዋሉ።ለምንም ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ በመሪ ሆነ ።እውር የመምራቱ ኋላፊነትም “ዝንጀሮ” ተብሎ ስም በወጣለት ብቸኛ ወንድ ልጃቸው ላይ ወደቀ።

የታወረ ዓይናቸውን ለማዳን ያላደረጉት ጥረት የለም። ያልተማሰ ስር፣ ያልተጨቀጨቀ ቅጠላ ቅጠል ያልኄዱበትና ያልከፈሉት ጠንቁዋይ የለም። በቃ የዓይን ነገር በተስፋ መቁረጥ ተከተተ።

ወይዘሮ አለቄ በጠንቋዮች የተነገረላቸውን ፈውስ ለብዙ ጊዜ ጠበቁት አልሆነም።ይልቁኑም የዓይናቸው ጥዝጣዜ ቀን እረፍት ሌሊት ደግሞ እንቅልፍ ነሣቸው። ልጆቻቸውን ደግሞ ቤት ያፈራውን አብስሎ የሚያበላቸው አጡ፣ ረሃብ በቤታቸው ተንሰራፍቶ ተቀመጠ።

አንድ ቀን የልጆቻቸውን ረሃብ ለማስታገስ እየተመሩ ከጓሮአቸው የሚገኝ የእንሰት ማሳ በመሄድ አንዱን እንሰት ለመጣል እየዳሰሱ በጦይሌ መቆፈር ጀመሩ። የሚቆፍሩትን ስር ሙሉ በሙሉ ነቅለው ሳይጨርሱ እጅብ ብሎ የተገጠገጠውን የእንሰት ቅጠል በዱላውና በእጁ እየከላ ከ_ከ_ከ_ከ እያደረገ አንድ ጎበዝ ብቅ አለ። ጆሮአቸውን ወደ ሰሙት ድምጽ አቅንተው” ማነው መንገድ በሌለበት አጥር ጥሶ የሚመጣው? እንዴት ቢደፍረኝ ነው? የሴት ጓሮ ነው ብሎ አይደል!?” አሉ ወይዘሮ አለቄ።

የጠዳ ልብስ የለበሰ፣ዠርጋዳ ቁመና ያለው፣ቀይ ሪዛም ሰው ፊት ለፊታቸው ቆሞ በቁዋንቁዋቸው “ጦሲ ማሮ!” ማለትም እግዚአብሄር ይማረዎት አለ።

…አሜን! ለመሆኑ ማነህ?!

…“እግዚአብሔር ይማረዎት ዓለሙ እባላለሁ”

…“ዓለሙ ማን?”

…“ከዚህ አራት ሰዓት እርቀት ላይ የምትገኘው የኡሞ አገሩ ዓለሙ አርሼ ነኝ”

…“ዝናህን አውቃለሁ…ዓይኔ ግን አያይህም”

…“ ጌታ ኢየሱስ ይማርዎት…ወደ እርስዎ የላከኝ ጌታ እየሱስ ይማርዎት”

…“እኔን መቼ አውቆኝ? …ለመሆኑ ምን ብሎ ላከህ?”

…“ዓይንሽን እፈውሳለሁ ብለህ ንገር አለኝ”

…“ እንዴት ሊሆን ይችላል?”

…“ ቢያምኑ ይሆናል”

“አኃ! ይህ ድንቅ ነገር ነው: ቆይ እዚህ ጥራጊ በምንጥልበት ጓሮ አትነግረኝም ወደ ቤት እንግባና ሁሉንም በአረፍታ ትነግረኛለህ…መቼ አውቆኝ ነው ለመሆኑ መልዕክት የላከብኝ? ……ልጃቸውን ና ምራኝ ብለው ተያይዘው ወደ ቤት ገቡ።

አቶ ዓለሙ ቤት ገብቶ ሳይቀመጥ የተላከበትን አደራ ለማስተላለፍ በኩታው ስር ከአነገተው ኮሮጆ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መዘዘ። ስለ በርጠሜዎስና ስለ ሌሎችም ጌታ እየሱስ ስለፈወሳቸው ሰዎች እየጠቀሰ ለወ/ሮ አለቄ ሰበከላቸው። የስብከቱ መቁዋጫ አንድ ነው “በርጠሜዎስን የፈወሰ እርስዎንም ይፈውሳል!”

መልካም ነው አሉ መበለቷ፣ መልካም ነው ግን ለእንዲህ ዓይነት ባለ መድሃኒት የምከፍለው ገንዘብ የለኝም፣ ለጠንቁዋይ እንኩዋን የከፈልኩትን ያገኘሁት በአሳር ነው አሉ።

ገንዘብ አያስፈልገውም፣እምነት ብቻ ይበቃል። እንኩዋን እርስዎ አይንዎ ብቻ የጠፋውን እኔን ልቤ የጠፋውን ሰው ልብ ሰጥቶ ከመቃብር ያወጣኝ ጌታ እየሱስ ነው! በማለት መልዕክተኛው ዓለሙ አርሼ የራሱን ታሪክ እንደቆመ ይተርክላቸው ጀመር። ታሪኩም እንዲህ ነበር።

ከመቃብር የወጣው ሰው

ዓለሙ አርሼ ከተወለደበት መንደር ወደ አዲስ አበባ ሥራ ፍለጋ የወጣው ገና አፍላ ወጣት እያለ ነበር። አዲስ አበባ ሥራ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ሙያ ተማረ ፣ ገንዘብ አጠራቀመ፣ ጥሪት ያዘ፣ ራሱን አሻሽሎ በአባቱ አገር ከታወቁት ባለጠጎች አንዱ ሆኖ ለመኖር ወደ ቀዬው ተመለሰ። ከመመለሱ በፊት ግን ወንጌል ሲሰበክ ለመስማት እድል አግኝቶ ነበር፣ ሊያምን ግን አልወደደም ነበር።

እንደ ምኞቱ ለመኖር ራሱን ሲያዘጋጅ እያለ የአባቶቹ የውቃቢ መንፈስ አረፈበት። የተለያዩ መስዋእቶች ለውቃቢው ሲገብር ያጠራቀመውን ጥሬ ገንዘብ ጨረሰ፣ ቋሚ ንብረቶቹንም እየሸጠ ያለውን ሁሉ አሟጠጠ።

የሰፈረበት አጋንንት ፀጉሩን እንዳይቆረጥ፣ጺሙን እንዳይላጭ ከለከለው። ዞማ ፀጉሩ አድጎ በጀርባው ወደቀ፣በግንባሩ አልፎ ተንጨፍርሮ አስፈሪ ፍጡር መሰለ።በዚህ አላበቃም ቤት እንዳይገባ ከለከለው፣መቃብር ማደር ጀመረ። የአገሩ ሰው በሞላ በአጭር ስለተቀጨው ጎበዝ አዘነ።ከጥቂት ወራት በሁዋላ ዓለሙ ለየለት፣እራቁቱን ሄደ ቀለቡን የዱር ፍራፍሬ እና ቅጠላ ቅጠል አደረገ፣ከአንዱ መቃብር ወደ ሌላው እየሄደ በመቃብሮች መሃከል እንደ በድን እየተጋደመ መኖር ጀመረ። አንዳንዴም ሲያሰኘውይጮሃል፡መላ የሌለው ጩሀት ዓይነት።

አንድ ቀን ግን የሆነ አንዳች ነገር ገፋፍቶ ወደ አባቱ ቤት መለሰው። ከጠጉሩ መርዘምና መንጨፍረር፣ከራቁትነቱና ከመቆሸሹ የተነሳ ዓለሙ አስፈሪ ፍጡር ብቻ ሳይሆን “ ራሱን ሞትን” ይመስል ስለነበር ማንም ሊቀርበው የሚደፍር አልነበረም።

የአባቱ ቤት በዚያን ጊዜ ማንም የማይኖርበት ወና ሆኖ ነበር። በዚያ ባዶ ቤት ውስጥ ገብቶ ዋለ ፣አመሸ ፣የአካባቢው ነዋሪ ጉድ አለ። እኩለ ሌሊት ላይ ግን ኡ…ኡ!…ኡ!…በኀይል መጮህ ጀመረ።

የሚተናነቀው ነገር ያለ ይመስል በጣዕር ይጓጉር ነበር። የመንደሩ አባወራዎች ተሰብስበው የሚያደርጉትን ተመካከሩ። ሁሉም የጠበቁት እንደሚሞት ስለሆነ የአባቱ ቤት ያለ ወራሽ ቀረ፣አርሼ ከሰረ እያሉ ለቅሶ ውን አወረዱት።

ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ጩሀቱ ጸጥ አለ። ዓለሙ እንደማይተርፍ የታወቀ ስለሆነ አስከሬኑን ለቀብር ለማዘጋጀት ሲሄዱ ግን ያጋጠማቸው ሌላ ዓለሙ ነበር።በደንብ የሚናገር ዓለሙ። ዓለሙም በዚያ ለተሰበሰበው ሰው እንዲህ በማለት ተናገረ።

“አንገቱን አንቆ ፣ከውስጤ ጎትቶ፣መንጥቆ ነቅሎ ጣለልኝ! …የበግ ቆዳ እንደሚገፈፍ የሆነ ነገር ገፍፎ ጣለልኝ! …እና እኔ ኢየሱስ ነኝ፣በቁም የቀበረህን ጥዬልሃለሁ፣በእኔ እመን…እኔ ማን እንደሆንኩ የሚያስረዳህ ወንጌልን የሚያስረዳህ ወንጌልን የሚናገር ሰው አቶ ጌንቦ የሚባልሰው በኦቾሎ (የስምንት ሰዓት የእግር መንገድ እርቀት ላይ) አለ፣……እዚያ ሄደህ የሚልህን ስማ መንገዱን እኔ እመራሃለሁ…እኔ እኔ ኢየሱስነኝ” አለኝ፤

በማለት የሌሊቱን ጩኅት ምንነትና ውጤት ለመንደሩ ኗሪዎች ነገራቸው። በማለዳው ልብስ ምግብ አመጡለት። ሰውነቱን ታጠበ፣ተላጨ፣ሰው ሆነ። በማግስቱ ጌታ ሂድ ወደ አለው የስምንት ሰዓት ጉዞ ተጉዞ ኦቾሎ ጸሎት ቤት አቶ ጌንቦ ደጅ ደረሰ።

ዓለሙ ኦቾሎ የደረሰው የማታ ማታ ነበር። አቶ ጌንቦ ከመንደሯ ሽማግሌዎች ጋር በዋርካ ጥላ ስር ተቀምጠው ሲያወጉ ጸጉረ ልውጥ ሰው በድንገት በመሃከላቸው ተግ ብሎ እጅ ነሳ።

…ከየት መጣህ…ማን ትባላለህ? አሉ አቶ ጌንቦ፦

…ከኡሞ አገር መጣሁ፣እየሱስ ክርስቶስ ወደ እርስዎ ላከኝ”

አቶ ጌንቦ ጨዋታቸውን አቁዋርጠው ያንን ሰው የእግዚአብሄር መላክተኛ ወደ ቤታቸው ይዘውት ገቡ። ሁሉን ነገራቸው፣ሁሉ በሁሉ የሆነውን የማዳን ወንጌል አጽንተው መሰከሩለት። በዚያን ዘመን እንደተለመደው ሁለት እጆቹን አንስቶ ክርስቶስ እየሱስን የግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ።ተገላገለ። አቶ ዓለሙ ኦቾሎ ተቀምጦ መጽሐፍ ቅዱስ እየተማረ ከመቃብር በላይ የሆነውን አዲስ ሕይወት በጣፋጭ የእግዚአብሔር ቃል እውነት አጣጣመ። በቀረው ዘመኑ ሁሉ ይህን ህያው የእግዚአብሔር ቃል ለመስበክ ሙሉ ጊዜውን ሰጠ። አገልግሎቱም በኅይል የተሞላ ሆነ።

ለአካባቢው የወንጌል አማኞች መሰብሰብያ በሆነችው የኦቾሎ ጸሎት ቤት ሓሙስ እና እሁድ መንፈሳዊ ፕሮግራም ይካሄዳል። በሩቅ ያሉት አማኞች ሓሙስ ለሚደረገው ፕሮግራም ረቡዕ ማታ፣ ለእሁዱ ደግሞ ቅዳሜ ማታ መጥተው ሲጸልዩ ያድራሉ። ዓለሙ ረቡዕ መጥቶ ባደረበት ሌሊት ያ የሚያውቀው ጌታ በክብርና በሞገስ እንደገና ተገለጠለት። ተገልጦም፦

“ አንተ በምትመላለስበት መንገድ ዳርቻ ሁለት ዓይኗ የጠፋ የሁለት ሕጻናት ልጆች እናት የሆነች አንዲት መበለት አለች። አንተ ለእሷ ወንጌልን ለመናገር ብትደፍር እኔ እፈውሳታለሁ…“ አለው።

“ጌታ የምትላትን ሴት አላውቃትም፣ ቤቷንም አላውቀውም።”

“እኔ እመራሃለሁ…አንተን የፈወስኩ እኔ እግዚአብሔር እሱዋንም እፈውሳለሁ”

ሓሙስ ማለዳ ከአምልኮ ፕሮግራም በሁዋላ አቶ ዓለሙ ወደ አገሩ ጉዞ ጀመረ። ወይዘሮ አለቄ መንደር ሲደርስ “አሁን ጎራ በል “ አለው ያ ድምጽ።ብዙ እንሰት በተተከለበትና ዝምታ በተጫጫነው ግቢ አቀና።የግቢውን በር አልፎ በቀጥታ ወደ እንሰቱ ተክል አለፈ:: በዚያን ወቅት ነበር ዓይነ ስውሯ መበለት እውር ድንብራቸውን ከእንሰት ጋር ሲታገሉ ያገኛቸውና “እግዚአብሔር ይፈውስዎት…“ የሚለውን ልዩ ድምጽ ፣ ሰምተውት የማያውቁትን ሰላምታ ዓይነት ያሰማቸው።

አቶ ዓለሙ ታሪኩን ሲተርክ የወይዘሮ አለቄ ልብ በእግዚአብሔር እውነት ተቀጣጠለች፣ አዳኙዋን በቶሎ ታገኝ ዘንድ።

“ እሽ…እንዲህ ከሆነ አምናለሁ” አሉ።

መሰረታዊ የአምልኮ መግለጫዎችን ይልቁኑም ስለ ጸሎት አበክሮ ነግሯቸው ተለያዩ።

ስድስት ቀን ጸለዩ፣ በሰባተኛው ቀን ጨለማው ነጋ! የወይዘሮ አለቄ ዓይን በራ!

ወይዘሮ አለቄን ሲመራ የኖረውና “ ዝንጀሮና ይቅርብህ “ ተብሎ የሚጠራው ብላቴናው የወይዘሮ አለቄ ወንድ ልጅ አምላክ በሰራው ተአምር ተደነቀ። ከእናቱ ጋር ኦቾሎ ጸሎት ቤት ሄዶ አመነ። ፊደልም ቆጥሮ በሶስት ቀን ጥናት ማንበብና መጻፍ ጀመረ፣ሕይወቱም ተለወጠ። የስሙ ነገር ግን ለዓለሙ ስሜት የጨፈገገ ሆነ፣ዝንጀሮ ብሎ ስም!

“ ከዛሬ ጀምሮ መርዶኪዎስ ብዬሃለሁ መርዶኪዎስ ጊሎ “ ሲል አዲስ ስም ዓለሙ አወጣለት”

አቶ ዓለሙ፣ አቶ ጌንቦ ፣ እማማ አለቄ ሁሉም ወደ አባታቸው እቅፍ አልፈዋል። ለታሪክ ይበቃል ብለው ሳይሆን የህይወት ምስክርነታቸውን ያካፈሉን ተራኪው የ65 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ መርዶኪዎስ አሁንም ከቤተ ክርስትያን አገልጋዮች አንዱ ናቸው።

ይህ ለናሙና ብቻ የተጠቀሰ ታሪክ ነው። ከዚህ ይልቅ ጥልቅነትና ረቂቅነት ያላቸው ድንቅና ተአምራት በጋሞ የወንጌል አማኞች መካከል ተፈጽመዋል። መንፈስ ቅዱስ በገዛ ፈቃዱ፣በወደደው መልኩ እየተገለጠ እንደ አቶ ዓለሙ አርሼ በመቃብር ውስጥ ያሉትን መቃብራቸውን ከፈተ። እንደ ወይዘሮ አለቄ ያሉትን የስጋና የመንፈስ ዓይኖቻቸውን አበራ። እንደ አባባ ጎባ ጎታ ያሉትን ከስጋና ከነፍስ ሞት አስነሣ። የገዛ ወንድሞቻቸውንም ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንዲያመጡ ለአገልግሎቱ ሾማቸው።

የዛሬውም የትናንቱም ታሪክ ባለቤት የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ስሙ የተባረከ ይሁን::

 

 

One comment

  1. Menbere Tenkir says:

    Thank you for sharing. May God bless you richly.Jesus is alive! I was very much uplifted by the story. May God’s grace rest upon you as you labor for His Kingdom.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *