Tsega.com – እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት – ከዶ/ር በቀለ በላቸው

Tsega.com – እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት – ከዶ/ር በቀለ በላቸው

www.Tsega.com: የጠለቀ መንፈሳዊ ጉዞ ለመጓዝና እየጨመረ የሚሄድ ርካታና እረፍት እንድናይ ካስፈለገ፣የክርስትና ሕይወት ትጋትን ይጠይቀናል(ዕብ 4:11)፡፡ በተለያየ ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃሉ እንደሚያስተምረን ትጋታችን እየጨመረ ሲሄድ፣የእግዚአብሔር ጸጋም በሕይወታችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ እናም ለመንፈሳዊ ነገር ያለን መሻት እያደገ ይሄዳል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ግሥገሣ ውስጥ ባለማሰለስ ስንገኝ፣እሱን ለማወቅ ያለን ራብ እየተጣጠለ ስለሚመጣ፣እየጨመረ ለሚሄድ ፍለጋ እንጠናከራለን፡፡ ይህንን በእንግሊዝኛው አገላለጽ positive vicious cycle ይሉታል፡፡ ማለትም ትጋቱ የጨመረ መንፈሳዊ ራብን ይወልዳል፤የጨመረው መንፈሳዊ ራብ ደግሞ ሌላ ከፍ ያለ ትጋትንና ግሥገሣን ይወልዳል፡፡ መቼም ይሄ ኡደት ማቆሚያ የለውም እኛ በሥጋዊ አካሄዶች እስካላጠፋነው ድረስ!

 

ከላይ ያለውን ሐሳብ በተግባር በሕይወቴ ስላየሁት፣በድፍረት ሕያው ምስክር ነኝ እላለሁ ፡፡ አዎ፣ከላይ ያለው ሐሳብ በቀድሞው ዘመን የነበረኝን ያላሰለሰ ትጋት ወደ ኋላ እንዳየው ያደርገኛል፡፡ ከነበረኝ ራብ የተነሣ በርከት ያሉ ጊዜያትን በጸሎትና ከቃሉ ጋር ተቆራኝቼ አሳልፍ እንደ ነበር ትዝ ይለኛል ፡፡ ስለዚህም ወደ ሕይወቴ የመጣው መንፈሳዊ ጉብኝት እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሕልውና ዘወትር በኃይል ይታወቀኝ ስለ ነበር፣ጸሎቴም ልዩ እንደ ነበር አስታውሳለሁ ፡፡ መጻሕፍት ቤት እንኳ ገብቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ማንበብ አቅቶኝ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ያ ትጋት በሕይወቴ ብዙ ፍሬን አፍርቷል ፡፡ አሁንም ድረስ ላለኝ የጸሎት መነሣሣት ትልቅ አስተዋፅኦን አድርጓል፤ጉብኝቱ የሚዳሰስ ነበረና ፡፡

 

በነገራችን ላይ እየጨመረ የሚሄድ የክርስትና ሕይወት ብዙ ግብዓቶችን ይፈልጋል ፡፡ መልካም የእምነት ውጊያንና ዲያቢሎስን በኃይል ጸንቶ መቃወም ይጠይቃል ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይታክቱ ማሰላሰልና በፊቱ ጥሩ የሆኑ ጊዜዎችን ማሳለፍ ግድ ይለናል ፡፡ ሁኔታዎችንና ሥጋችንን ሳናዳምጥ የሚከፈሉ ዋጋዎችን እንደ ጌታ ፈቃድ መክፈልን ይጠይቀናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ አለው፤ደግሞም በረከት አለው፡፡ ትእዛዙን በእግዚአብሔር ጸጋ ተደግፈን ሳንፈጽምና ሳናከናውን፣በረከት መጠበቅ ሞኝነት ነው ፡፡ ስለዚህ ጌታ በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ እንዲባርከን፣ መታዘዝ ልንወስደው የሚገባን እርምጃ ነው፡፡

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕይወቴን የቀየረና ብዙ ቦታ ደጋግሜ የምጠቅሰውን መርሕ እዚህ ጋ ልጥቀስ፡፡ሦስት በተሰናሰለ መንገድ የተቀመጡ ድርጊቶች በውጤት ሂደት እንዲህ ተቀምጠዋል፡-

 

               ድርጊት(Action)——->ልማድ(Habit)——->ጠባይ(character)

 

ይህንን መርሕ ለመግለጽ ጸሎትን እንደ ምሳሌ ልውሰድ ፡፡ ጸሎትን ደጋግመን ስናደርገው ወደ ልማድነት ይቀየራል ፡፡ በሕይወታችን ልማድ እየሆነ የመጣውን ተግባር እየጨመርን ደጋግመን ስናደርገው፣ጠባያችን ወይም መገለጫ ባሕርያችን ይሆናል ፡፡ ከዚያማ ውጤቱ እንዲህ ይሆናል፡-

  • “መጸለይ እንጂ አለመጸለይ አንችልም፡፡”
  • “በፊቱ መሆን እንጂ አለመሆን ያቅተናል፡፡”

እጅግ ሊጓጓለት የሚገባ ድንቅ ለውጥ!

 

የላይኛውን ሐሳብ የሚደግፉና የክርስትና ሕይወት እየተቀጣጠለ፣እያደገና እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት እንደ ሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ክፍሎች አሉ ፡፡ ለምሳሌ ሦስቱን ልጥቀስ፡-

 

  • “እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ” (ኤፌሶን 3፥19)
  • “በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ” (ሮሜ 12፥11)
  • “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” /ብዙ የሚያሰክሩ ነገሮች እንዳሉ ልብ ይሏል/(ኤፌሶን 5፥16-20)

 

የእግዚአብሔር ሰው ስሚዝ ዊግልስዎርዝ እንዲህ ብሎ ነበር፡-“If you are in the same place today as you were yesterday, you are a backslider.”(ትርጉሙ፡-በዛሬው ቀን ትላንትና የነበርክበት ቦታ ላይ ከተገኘህ የኋሊት እየሄድክ ነው)

 

በተሰጠ ማንነት፣ልባችን መሉ በሙሉ በጌታ ላይ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት ፍለጋ(craving) እና ትጋት ስንቀጥል፣የጌታ አብሮሆት ከመቸው በሚበልጥ ሁኔታ በሕይወታችን ዕውን ይሆናል ፡፡ ከዚህም የተነሣ የምናገኘው የመጀመሪያው በረከት በቃላት ልንገልጸው የማንችለው ሰላም፣መረጋጋትና ደስታ ይሆናል ፡፡ መንፈሳዊ መረዳታችንም እየጨመረ ስለሚሄድ፣ጌታን በሚገባ እያወቅነው እንመጣለን፡፡ስለዚህ ለውጣችን ወደ ኋላ የማይቀለበስና ዘላቂ ይሆናል ፡፡ መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በጨመረ ሁኔታ እየተከፈቱ ስለሚመጡ፣ብዙ ረብ የሌላቸውን ነገሮች የመጣል መነሣሣትና አቅም እያገኘን እንመጣለን ፡፡

 

እንደዚህ በጽናት ሳናሰልስ የጌታን ፊት በጨመረ ሁኔታ በፈለግን ቁጥር፣የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን እየጨመረ ስለሚሄድ፣ብዙ ቀንበሮች ከሕይወታችን ይሰበራሉ ፡፡ ስለዚህም“ሸክሙ ከጫንቃህ ቀንበሩም ከትከሻህ ላይ ይሰበራል” የሚለው ቃል በሕይወታችን ይፈጸማል (ኢሳ.10፡27)፡፡ እናም ከበፊቱ ይልቅ በሕልውናው ውስጥ መቆየት አያስቸግረንም ፡፡ ብዙ ሰዓት በፊቱ መሆንም ያለ ጥርጥር ፈቃዳችን ይሆናል ፡፡ እሱን በአካል ባናየውም እንኳ፣በመንፈስ እያየነው በጨመረ ሁኔታ እንወደዋለን፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላልና፡-

 

“እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል” (1 ጴጥሮስ 1፥8-9)

 

አዎ፣በጨመረ ሁኔታ በመንፈስ እያየነው ሰንቀጥል፣ልባችንም በፍቅሩ እሳት በጨመረ ሁኔታ ስለሚጋይ፣ጉገታችንና ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ሁልጊዜም በፊቱ መገኘት ይሆናል ፡፡ ቢሆንም ይሄ ውጤት በቀላል እንደሚመጣ ማሰብ የለብንም ፡፡ በጌታ ጸጋ ብዙ ትጋት፣ብዙ ፍለጋ፣ብዙ ቁፈራ፣በጌታ ፊት አዘውትሮ መሆንን ይጠይቀናል ፡፡

 

ለዚህ ሐሳቤ ጥሩ እይታ የሚሰጠን ኢዮብ 28፥1-11 ነው ፡፡ ይህ የምንባብ ክፍል የማዕድን ሠራተኛ ከባዶ ተነሥቶ የሚያደርገውን ግሥገሣ ነው የሚያሳየው ፡፡ “ዓይኑ ዕንቁን እስክታይ ድረስ”“የተሸፈነው ነገር ወደ ብርሃን እስኪወጣ ድረስ” ይተጋል ፡፡ እጁን ወደ ቡላድ ድንጋይ ይዘረጋል ፡፡ መጨረሻ ላይ ከብዙ እልህ አስጨራሽ ትግልና ጉዞ በኋላ የከበሩ ማዕድናትን ያገኛል፤ክፍሉ የልፋቱን ውጤት እንዲህ ይገልጸዋልና ፡-

“ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፤ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል። ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች   ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።”(ቁ.9-11)

አዎ ይህ ክፍል ምሳሌያዊ በሆነ አገላለጽ፣እንደ ማዕድን ሠራተኛው ያለ መታከት እንድንተጋና የጌታን ፊት እንድንፈልግ ያስተምረናል ፡፡ በቃሉ ውስጥ፣በጸሎት ኅብረት ውስጥ፣በትምህርት ውስጥ፣በጥሞና ጊዜና በተለያዩ ፕሮግራሞች ውስጥ፣ሳናሰልስ እንድንፈልገው ይጠቁመናል፡፡

 

የእግዚአብሔር ቃል ተግተው “የሚሹኝ ምስጉኖች/የተባረኩ ናቸው” (ምሳሌ 8፡34) ይላልና፤ እናንተም ትጠሩኛለችሁ፤ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፣እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፣በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፡፡” (ኤር.29፥13-14) ይላልና ጨክኖ የጌታን ፊት የሚፈልግ ሰው ይዋል ይደር እንጂ፣የእግዚአብሔር በረከት ታገኘዋለች፡፡

 

አዎ፣ጌታ አጥብቀው ለሚሹት ሰዎች በእርግጥ ይገለጣል ፡፡ ጉብኝቱ ደግሞ ልባችን ላይ የሚያመጣው ለውጥ ቀላል አይሆንም ፡፡ የበለጠ እንድናየው፣የበለጠ በእርሱ ላይ እንድንደገፍና እንድንጠጋው ያደርገናል ፡፡ በተጨማሪም ጌታ ተገልጦ ሕይወታችንን ሲጎበኝ የሚመጣው ለውጥ ለሌሎች በረከት ያደርገናልና በትጋትና በጨመረ ሁኔታ ተግተን እንፈልገው!

 

ጌታ ሆይ እርዳን!!

 

“አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፣ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ ። ወንድሞች ሆይ፣እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ፊልጵስዩስ 3፡7-13)

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *