ታላቁ ስጦታ – ከመልሕቅ መጽሄት

ታላቁ ስጦታ – ከመልሕቅ መጽሄት

ነገሩ እንዲህ ነው። ቢል የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ጥቂት ወራት ሲቀረው ወደ አባቱ ቀረብ ብሎ “አባቴ ሆይ ትምህርቴን ስጨርስ የምትሸልመኝ ምንድነው?” በማለት ይጠይቃል። አባትየውም ቢል ጎበዝ ተማሪ እንደሆነ ስለሚያውቅ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመረቅ አንድ ዘመናዊ መኪና ሊገዛለት ቃል በመግባት በዕለቱ መኪናውን የሚገዛበትን ቼክ እንደሚያስረክበው ይነግረዋል።

በቀሩት ወራት ቢል ስለሚሰጠው ቼክ ስለሚገዛው መኪና እያሰላሰለ ከቆየ በኋላ በግዜው ተመርቆ ቤቱ ገባና ከአባቱ የሚበረከትለትን የቼክ ስጦታ መጠባበቅ ጀመረ። በዚህን ግዜ አባትየው ልጁን በደስታ ተቀብሎ ከሳመውና መልካም ምኞቱን ሁሉ በአባታዊ ፍቅሩ ከገለፀለት በኋላ አንድ ትልቅ የታሸገ ፖስታ ያበረክትለታል።

ቢል ከአባቱ የተገባለትን ቃል ስላስቸኮለው ወዲያው የታሸገውን ፖስታ ሲከፍት ውስጡ ያገኘው መጽሀፍ ቅዱስ ነበር። የተሰጠው ስጦታ የስጦታዎች ሁሉ ቁንጮ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ መደሰት የነበረበት ቢል ተበሳጭቶ ስጦታውን በመወርወር ቤቱን ጥሎ ጠፋ። ወዴት እንደሄደ ባለመናገሩ ቤተሰቦቹ ሁሉ በጣም አዘኑ። ሳያገኙትም ብዙ ግዜ ቆዩ። ከረጅም ግዜ በኋላ የቢል አባት ይሞታል። ልጁ ቢልም ያባቱን መሞት ሰምቶ ወደ ቤተሰቡ በመምጣት ካዘነና ካለቀሰ በኋላ ቤቱን እየተዘዋወረ ሲመለከት ለምርቃቱ ከአባቱ የተበረከተለትን መጽሐፍ ቅዱስ መደርደሪያ ላይ ይመለከታል። በዚህን ግዜ “ይህ ከአባቴ የተሰጠኝ ስጦታ ከእኔ ጋር መሆን አለበት”©ብሎ አነሳውና ሲከፍተው ውስጡ አንድ ቼክ አገኘ። በላዩም ከአባቱ ቃል የተገባለትን መኪና መግዛት የሚችል መጠን ገንዘብ ተጽፎበት ነበር።ከዚህ በኋላ ቢል ቀድሞ ባደረገው ስህተት ተፀጽቶ የአባቱን ስጦታ አክብሮ በመቀበል ብሩን ለችግረኞች ከሰጠ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሱን በየግዜው በማንበብ መንፈሳዊ ሕይወቱን መምራት ጀመረ።

በምድር ላይ ለሰው ልጅ የተሰጠ ትልቁ ስጦታ መፅሐፍ ቅዱስ ነው። ይህንንም ስጦታ የሰጠን ሰማያዊ አባታችን ልል እግዚአብሔር ነው። መፅሐፍ ቅዱስን መመሪያችን ብናደርግ ባዶነታችን ይሞላል፤ ችግራችን ይቃለላል፤ ከበሽታችን እንፈወሳለን፤ ፍም ንህ እንሆናለን። በሀብት ብንከብር ፤ በዕውቀት፣ በጉልበት ፣በስልጣን ታዋቂዎች ብንሆን የእግዚአብሔር ቃል በኛ ዘንድ ከሌለ ሁሉ ነገራችን ከንቱ ነው። የእግዚአብሄር ቃል ሕይወት ነው። የእግዚአብሄርን ቃል እናንብብ እንስማ፣ በእግዚአብሄር እንመራ። ለሁሉም አምላካችን ይርዳን።

አሜን!

“ከአዕላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ህግ ይሻለኛል”©መዝ 118 ፦ 72

ከአነበብኩት አብርሃም ዳምጤ Saint Louis Missouri

 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *